በፍቅር ተደምረን፣ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ማስመዝገባችንን እንቀጥል!

ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ የአቋም መግለጫ-ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም.

በፍቅር ተደምረን፣ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ማስመዝገባችንን እንቀጥል!

“በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር“ በሚል መሪ መልዕክት አዲስ መንፈስ ታጥቀን፣ አዲስ ተስፋ ሰንቀን መጪውን አዲስ ዓመት በደስታ ለመቀበል እየተዘጋጀን ባለንበት በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አገራችን ለተያያዘችው ሪፎርም እየሰጠ ያለው እውቅና እና ድጋፍ በእርግጥም መጪው ጊዜ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ብሩህ መሆኑን ከወዲሁ እያመላከተን ይገኛል።

በያዝነው ነሃሴ ወር ውስጥ ብቻ እንደተመለከትነው፣ የዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዓለም አቀፍ ትብብር ጉዳዮች ሚኒስትር፣ እንዲሁም በፓርላማ አባል ክሪስ ስሚዝ የተመራው የአሜሪካ ልዑካን ቡድን፣ የቪየትናም ፕሬዚዳንት እና የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ሌሎች በርካታ ልዑካን አገራችንን ጎብኝተው ተመልሰዋል።

የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አገራችን በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ላካሄደቻቸው ሪፎርሞች እና ከኤርትራ ጋር ለፈጠርነው ሰላም ዕውቅና እና ድጋፍ በመስጠት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አገራቸውን እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርበዋል።

የፊታችን ነሃሴ 28 እና 29 ቀን በሚካሄደው የቻይና እና የአፍሪካ የወዳጅነት እና የትብብር መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ ቤጂንግ የሚያቀኑት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቆይታቸው ከቻይናው ፕሬዚዳንት ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነቶች የበለጠ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ።

ከላይ የተገለጹት እና ሌሎችም የበርካታ አገራት ተወካዮች ያካሄዷቸው ጉብኝቶች በአገራችን እየተካሄደ ላለው ለውጥ የተሰጡ እውቅና እና ድጋፍ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል። በጉብኝቶቹ ወቅት እንደተገለጸውም አገራቱ ከአገራችን ጋር በንግድ፣ በግብርና፣ በአቅም ግንባታ፣ በትምህርት፣ በኢንቨስትመንት፣ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና የሁለትዮሽ የትብብር ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት እና ግንኙነቶቻቸውን ለማጠናከር ፍላጎቶቻቸውን ገልጸዋል። በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ የዓለም ታዋቂ ኩባንያዎች ቁጥርም እየተበራከተ መጥቷል።

በአጠቃላይ፣ በጣም አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ በዲፕሎማሲው መስክ ያካሄድናቸው እንቅስቃሴዎች በርካታ ሲሆኑ የተገኙት ድሎችም የዚያኑ ያህል ብዙ እና ከአገራችን ጥቅም አንጻር ሲታዩ መሰረታዊ ሊባሉ የሚችሉ ናቸው።

በተለይም የምንገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በቋንቋ፣ በባህልና በታሪክ የተሳሰሩ በርካታ አገራትን ያቀፈ፣ ሆኖም ግን ከጦርነት እና ከመቆራቆስ ተነጥሎ የማያውቅ እንደመሆኑ መጠን ከአካባቢው አገራት ጋር የፈጠርናቸው ግንኙነቶች የቀጠናውን ነባራዊ ሁኔታ ከመሰረቱ መለወጥ የሚያስችሉ ናቸው። ግንኙነቶቻችን የጋራ ወደቦችን ከማልማትና ከመጠቀም እስከ ኢኮኖሚያዊ ውህደት የሚያልሙ ናቸው።

በተለይም ደግሞ፣ ከእኛ ጋር በቋንቋ፣ በባህልና በታሪክ የጠነከረ ትስስር ካላት ኤርትራ ጋር የተደረገው ስምምነት አንድ ነገር ሆኖ ስምምነቱ የተደረሰበት አካሄድ ደግሞ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አድናቆት ያተረፈ፣ የምስራቅ አፍሪካን የፖለቲካ ሁኔታ በእጅጉ መቀየር የሚያስችል እና ለሌሎች አገራት በተምሳሌትነት የሚወሰድ ሆኗል።

እነዚህን እና መሰል ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ስንዘክር ሊመዘገቡ የቻሉበትንም ምክንያት በውሉ መገንዘብ ያሻል። ድሎቹ የተገኙት በቅድሚያ በእኛ ኢትዮጵያውያን መካከል ተተክሎ የቆየውን የጥላቻ ግንብ አፈራርሰን በምትኩ የፍቅር ድልድይ ገንብተን ሁላችንም በአንድ ልብ ለአንዲት ጠንካራ አገር ግንባታ በጋራ በመሰለፋችን የተነሳ መሆኑን ማጤን ያሻል። ይህንን ዕውነታ መገንዘባችንም የተጀመረውን ሂደት አጠናክረን ለመቀጠል ያግዘናል።

ትናንት ተራርቀን እንደጠላት እንተያይ የነበርን የአንዲት አገር ልጆች ዛሬ በይቅርታ እና በፍቅር ተደምረን የጋራ ቤታችንን ለመገንባት የጀመርነው ጥረት በእርግጥም አገራዊ ጥንካሬን እንደፈጠረልን እና ይህን መሰሉ ጥንካሬያችንም የዓለምን ከበሬታ ሊያተርፍልን እንደሚችል በተግባር ያረጋገጥንበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል።

በመሆኑም የጀመርነውን የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ አጠናክረን መቀጠል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። የጀመርነውን ለውጥ በማፋጠን ያሰብነውን አንዲት ጠንካራ አገር የመፍጠር ውጥናችን ሊሳካ የሚችለው በቀዳሚነት ሰላማችንን ማረጋገጥ ስንችል ነው።

ለዚህ ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች ብቅ ጥልቅ በማለት ገጽታችንን ለማጠልሸት እየተፈታተኑን ያሉትን አፍራሽ አዝማሚያዎች እና ድርጊቶች በአስቸኳይ ማስቆም ይገባናል። ይህን ማድረግም የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አገራዊ ግዴታ እና ሃላፊነት በመሆኑ ሰላማችንን ለመጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንድንተጋ የኢፌዴሪ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።