መመዘን ያለብን በዘራችን ሳይሆን በስራችን መሆን አለበት – ግርማ_ካሳ

አንድ ጊዜ አንድ የገዥው ፓርቲ ደጋፊ የሆኑ ጦማሪ “አንዳንድ ሰዎች «ብሄር ..?» ተብለው ሲጠየቁ «ኢትዮጵያዊ!!!…» እያሉ የሚመልሱት፣ የራሳቸዉን ማንነት የኢትዮጵያ ማንነት አድርገው ያስቀመጡና በራሳቸው ማንነት የሌሎቹን ለመጨፍለቅ የሚያልሙ – የቅዠት ታንኳ ቀዛፊዎች ናቸው…. ተዛብታችሁ ሌላንም ለማዛባት ለምትፈልጉ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ዜግነት እንጂ ብሄር አይደልም። ኢትዮጵያ ሃገር እንጂ የአንድ ሕብረተሰብ ክፍል መለያ አይደለም።” የሚል አባባል ፌስቡክ ላይ ለጥፈው አንብቤ ነበር።

በአንቀጽ 39 ንኡስ አንቀጽ 5 ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሕገ መንግስቱ “በዚህ ሕገ መንግስት ዉስጥ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ሕዝብ ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸዉን ባህርይ የሚያሳይ ማህበረሰብ ነዉ። ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልዉና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የስነ-ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛዉ በተያያዘ መልክአ ምድር የሚኖሩ ናቸው” ሲል ለብሄር የተሰጠው ትርጉምና ለብሄረሰብ የተሰጠው ትርጉም አንድ አይነት እንደሆነ ያሳያል። በአጭሩ ብሄር ማለት ብሄረሰብ ማለት ነዉ በሕገ መንግስቱ መሰረት።

ብሄር በእንግሊዘኛ ኔሽንስ (nations) ማለት ነዉ። «ዩናይትድ ኔሽንስ» (United Nations) ስንል የተባበሩት መንግስታት (የተባባሩት አገሮች ማለታችን ነዉ) ። እንደሚገባኝ ኢትዮጵያ እንጂ፣ ኦሮሞ፣ ወይንም፣ ትግሬ ወይንም ወላይታ የተባበሩት መንግስታት አባል አይደሉም።

«ብሄር» የሚለዉን ቃል የመጀመሪያ አመጣጥ ስንመለከት ፣ ከግእዝ የተወሰደ እንደሆነ እንረዳለን። ትርጉሙም በግእዝ አገር ማለት ነዉ:: ኢሕአዴግን እና ኦነግ በሕገ መንግስቱ ሲያረቁ፣ “ብሄር” የሚለዉን ቃል ያኔ የወሸቁት፣ ኢትዮጵያን እንደ አንዲት አገር ሳይሆን የተለያዩ የአገሮች ስብሰብ እንደሆነች ለማሳየት፣ በፈለጉ ጊዜ ደግሞ ከኢትዮጵያ ለመለየት አማራጭ እንዲኖራቸው ከመፈለግ የተነሳ ነው የሚል አስተሳሰብ ነው ያለኝ።

ፕሮፌሰር ተኮላ ሃጎስ ደግሞ ብሄር ብሄረሰብና ሕዝብ የሚለውን ለምን ሕገ መንግስቱ ዉስጥ እንደገባም ሲጽፉ የሚከተለዉን ነበር ያሉት፡

“The phrase “the nations, nationalities and peoples” thus found in the Ethiopian Constitution is a legacy from the writings of immature and juvenile diatribe of badly educated and socially disfranchised and radicalized students of Haile Selassie I University of the 1970s. It is the ersatz voice of Meles Zenawi forcing himself through the 1995 Constitution on the People of Ethiopia his narrow and ignoramus ideas on the history of Ethiopia and the process of nation building”

ስለዚህ «ብሄርህ ምንድን ነዉ ?» ተብሎ አንድ ሰው ሲጠየቅ «ኢትዮጵያዊነት» ብሎ ከመለሰ፣ በትክክለኛዉ የግእዝ አተረጓጎም ወይም በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ብሄር የሚለው ቃል ካለው አጠቃቀም አንጻር፣ ትክክለኛ መልስ ነው።

«ብሄረሰብህስ ምንድን ነዉ ? » የሚል ጥያቄ ቢነሳስ ? አንድ መርሳት የሌለብን ነገር አለ። አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ የተደባለቀ ነዉ። ሰሜን ጎንደና ሰሜን ወሎ ከሄዳችሁ ትግሪኛ ተናጋሪዉና አማርኛ ተናጋሪዉ ተደበላልቋል። ኦሮሚያ ዉስጥ በሸዋ፣ በሰሜን እና በምስራቅ ወለጋ..፣ አማራዉ ክልል ደግሞ በወሎ ፣ ኦሮሞኛ ተናጋሪው ከአማርኛ ተናጋሪው ተደባልቋል። በምስራቅ ሃረርጌና በባሌ ደግሞ ሶማሌዉና ኦሮሞዉ የተደባለቀበትም ሁኔታ አለ። በወሊሶ አካባቢ ጉራጌውና ጨቦ ኦሮሞው የተዛመደ ነው። በደቡብ ክልል ከሄድን፣ ወላይታዉ ከሲዳማው፣ ከንባታዉ ከሃዲያዉ …ሁሉም ተበራርዟል። ስለዚህ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን የብዙ ብሄረሰቦች ድብልቅ ናቸው ቢባል ስህተት ነው ሊባል አይችልም። በመሆኑም ሚሊዮኖች «ብሄረሰብህ ምንድን ነዉ?» ተብለው ሲጠየቁ እዚም እዚያም በመሆናቸው፣ ለመመለስ ከመቸገራቸው የተነሳ ፣ በአጭሩ በብሄረሰባቸው ወይንም በዘራቸው ሳይሆን በኢትዮጵያዊነታቸው መለየትን ቢመርጡ ሊወቀሱ አይገባም።

ከነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ነኝ። የአገዛዙ ካድሬዎች ወይንም እንደ ኦነጋዉያን ያሉ የአንድ ብሄረሰብ አክራሪ ፖለቲከኞች፣ ኢትዮጵያዊያን፣ ብሄራችን ኢትዮጵያዊነት ነው ማለታችንን፣ የሌሎችን ማንነት ለመጨፍለቅ እንደመሞከር አድርገውም ይወስዱታል። አንድ ሰው «ኦሮሞ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ ወዘተረፈ » የማለት መብቱ ከተከበረለት፣ ሌላው «አይ እኔ በዘሬ መለየት አልፈልግም፣ በኢትዮጵያዊነቴ ነዉ መለየት የምፈልገው » ካለ የርሱስ መብት ለምን አይከበርለትም ? ኦሮሞ፣ ወይም ትግሬ ፣ ወይም አማራ ያለመባል መብቱ መጠበቅ የለበትምን? ሕወሃት/ኦሕዴድ ኢሕአዴግ በአሁኗ ኢትዮጵያ ግን ይሄ መሰረታዊ መብት እየተጠበቀ አይደለም። እያንዳንዱ ዜጋ፣ እነርሱ ብሄር ብሄረሰብ የሚሉት አንዱ የዘር ጆንያ ዉስጥ መግባት አለበት። ያ ካልሆነ መታወቂያ እንኳ ማግኘት አይቻልም። (በነገራችን ላይ በቅርቡ አዲስ አበባ ዘር ወይም እነርሱ ብሄር የሚሉትን ነገር ከመታወቂያ ለማንሳት መወሰኑን ወይም እቅድ እንዳለ፣ አላረጋገጥም ሰምቻለሁ። የሰማሁት እዉነት ከሆነ ትልቅ እርምጃ ነው። በሌሎችም አካባቢዎች መሆን ያለበት ነው)

ለአገራችን “ዘር ላይ ማተኮር ሳይሆን፣ የሚያስተሳሥረን አንድነታችን ላይ ማተኮር ነው የሚሻለው። መመዘን ያለብን በዘራችን ሳይሆን በስራችን መሆን አለበት” እላለሁ።