የአማራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ያደረጉትን ጥሪ የተጣመመ ነዉ

[addtoany]

የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ትግራይ ዉስጥ ደረሰ በተባለ ግድያና ግፍ ተሳትፏል መባሉን የአማራ ክልል አስተባበለ። የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቲኒዮ ብሊንከን ምዕራባዊ ትግራይ ዉስጥ «የዘር ማፅዳት» ግፍ ተፈፅሟል ብለዉ ነበር።

ብሊንከን ሹመታቸዉን ለሚያፀድቀዉ ለሐገራቸዉ ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ ባደረጉት ንግግር ትግራይ ዉስጥ ተፈፀመ ባሉት በደል የአማራ ክልል ኃይላት መካፈላቸዉን አስታዉቀዉም ነበር።

የአማራ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ግዛቸዉ ሙሉነሕ ዛሬ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰጡት መግለጫ ትግራይ ዉስጥ የዘር ማፅዳትና ሕዝብ የማፈናቀል እርምጃ ተወስዷል መባሉን «ፕሮፓጋንዳ» በማለት አጣጥለዉታል።

የአማራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ያደረጉትን ጥሪም አቶ ግዛቸዉ «የተጣመመ» ብለዉታል። አቶ ግዛቸዉ አክለዉ፣ የአማራ ኃይል የሠፈረበት ግዛት አሁን የአማራ ሆኗል፤ በታሪክም የትግራይ ሳይሆን «የአማራ ነዉ።» ማለታቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ጠቅሷል።