መንግስት ጥያቄያችንን ካልመለሰ በምርጫ አንሳተፍም፤ እጩም አላስመዘገብንም – ኦፌኮ

May be an image of 2 people and text that says 'OROMO FEDERALIST CONGRESS OFC DDD Oromo Federalist Congress -OFC'የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) በመጪው አገራዊ ምርጫ እንደማይሳተፍ የሚገልጹ መረጃዎች ዛሬ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ተሰራጭተዋል። ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ ማምሻውን የፓርቲውን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን እና የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊን አቶ ጥሩነህ ገመታን አነጋግሯል።

እነዚህ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በትናንትናው ዕለት የጠየቋቸው ጥያቄዎች ባልተመለሱበት ሁኔታ በምርጫው እንደማይሳተፉ፣ ጥያቄዎቹ ምላሽ ካገኙ ግን ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ለኢትዮጵያ ቼክ እንደተናገሩት ፓርቲያቸው በተደጋጋሚ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ ስላላገኙ እስካሁን ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አላስመዘገበም።

ጥያቄዎቹ ምላሽ ካገኙ በምርጫው ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር መረራ “ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ አሁን የጠየቅናቸውን ጥያቄዎች በአንድ ቀን፣ ወይም በሁለት ቀን መፍታት ይችላል። ገዢው ፓርቲም ሆነ ምርጫ ቦርድ ያንን እርምጃ ከወሰዱ ምርጫውን የማንቀጥልበት ምክንያት የለም” በማለት ለኢትዮጵያ ቼክ አብራርተዋል።

የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ በበኩላቸው “የተሻለ አሰራር ከመጣ ነገም ቢሆን ተሳታፊዎች ነን፤ የጠየቅናቸው ጥያቄዎች ከተመለሱ እኛ ምን ችግር አለብን? እንሳተፋለን። [ያልነው] አንሳተፍም ሳይሆን ተገፍተን ወጥተናል ነው፤ ጫና ተደርጎብን ወጥተናል ነው፤ ለመሳተፍ ብቻ አይደለም የምንፈልገው፤ የኛ ሀሳብ አሸናፊ ከሆነ አሸንፈን ሀገር ለመምራት ነው” ሲሉ ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።

ኦፌኮ በምርጫው ለመሳተፍ ሳንካ ሆነውብኛል ያላቸው ችግሮች መፍትሄ ባላገኙበት ሁኔታ ግን በምርጫው እንደማይሳተፍ አቶ ጥሩነህ ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በቅርቡ በፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ስም እና ፎቶ ተመሳስሎ የተከፈተ ሀሰተኛ ገፅ እንደሆነ አሳውቀን የነበረው የትዊተር አካውንት ማምሻውን ኦፌኮ ከምርጫው ራሱን እንዳገለለ ፅፏል። ይህ 4,000 ገደማ ተከታይ ያለው የትዊተር አካውንት የርሳቸው እንዳልሆነ በድጋሜ ልንገልፅ እንወዳለን።