በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ ሀርቡ ቀበሌ ከ10 በላይ ሰዎች በሽፍቶች መገደላቸው ተገለጸ

በትላንትናው ዕለት ምሽት በመተከል ዞን ከወንበራ 35 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሀርቡ ቀበሌ ከ10 በላይ ሰዎች በሽፍቶች መገደላቸውን ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የወንበራ ወረዳ ሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ባለሙያ ነግሮናል።

የወንበራ ወረዳ አጎራባች ወረዳ የሆነው የጓንጓ ወረዳ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ብርሀኑ መኮንን በበኩላቸው በሀርቡ ቀበሌ 10 ሰዎች መገደላቸውን ማረጋገጣቸውን ነግረውናል።

ይህ ቁጥር መረጃው እስከተጠናቀረበት ድረስ ያለ ሲሆን ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችልም ተነግሯል።

ከዚህ በተጨማሪም 7 የፖሊስ አባላት፤1 አመራር እና 1 የጸጥታ ባለሙያ የጸጥታውን ሁኔታ ሊያስከብሩ በሄዱበት በሽፍቶች መታገታቸው ተሰምቷል።

9 ክላሺንኮቭና 2 ሽጉጥ በሽፍቶች እንደተወሰደባቸው የተገለጸ ሲሆን እስካሁንም ሰዎቹ አልተለቀቁም ተብሏል።

ከዚህ ቀደም ከሌሎች አካባቢዎች የተሻለ ሰላም የነበረባት ወንበራን ለመረበሽ እንቅስቃሴዎች እየታዩ እንዳሉም ተገልጿል።

በብዙ ወረዳዎች ላይ የጉሙዝ ሽፍቶች እጅ እየሰጡ ነው ቢባልም የአካባቢው ነዋሪ ግን ጥርጣሬ እንዳለው ከወረዳው ኮሙንኬሽን ሰምተናል።

ከመተከል ዞን ተፈናቅለው ቻግኒ የሚገኙት ተፈናቃዮች ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚሊሻ ስልጠና እየወሰዱ ነው የተባለ ሲሆን በማንዱራ ወረዳ በሁለት ዙር 1 ሺ 145 ተፈናቃዮች መሰልጠናቸው ከሰሞኑ በክልሉ መንግስት መገለጹ ይታወሳል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረ የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት በኮማንድ ፖስት መመራት ከጀመረ ወራቶችን ያስቆጠረ ሲሆን ኮማንድ ፖስቱ ግድያ ተፈጸመ በተባለበት ቀበሌ ስራ መጀመሩን ከአይን እማኞች ሰምተናል።

የቤኒሻንጉል ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሌ ሀሰን መከላከያ ሰራዊት 2 ሺህ ታጣቂዎች እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ማድረግ ችሏል ሲሉ መናገራቸውን የክልሉ የኮሙንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።