ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ673 የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቁሳቁስ ማድረሱን ገለጸ፡፡

የምርጫ ቁሳቁስ ማጓጓዣ ችግር አፋጣኝ እልባት ካላገኘ አገር አቀፉን የምርጫ ሂደት ሊያስተጓጉል ይችላል ሲል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ቁሳቁሶችን እስካሁን በራሱ አቅም ተደራሽ ለማድረግ ባደረገው ጥረት በ673 ቦታዎች ማድረሱን አስታወቀ፡፡

ቦርዱ በእጩዎች ምዝገባና ተያያዥ ሂደቶች ዙሪያ ለመራጮች እየሰጠ ያለውን መረጃ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንዳስታወቀው በተለያዩ ክልላዊ አስተዳደሮች የምርጫ ክልሎችን ለመክፈት እና ቁሳቁሶችን ለመጓጓዝ የሚደረገው ጥረት በተፈለገው ፍጥነት እየሄደለት አይደለም፡፡

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱኳን ሚደቅሳ እንደገለጹት የምርጫ ክልሎችን ለመክፈት እና ቁሳቁሶችን ለመጓጓዝ የሚደረገው ጥረት የተስተጓጎለው የመከላከያ ሰራዊቱ በህግ ማስከበር ስራ መሰማራቱን ተከትሎ በተፈጠረ ክፍተት ነው፡፡

በየክልሎቹ ባለ የተለያየ መልከአምድራዊ አቀማመጥ ሳቢያ ቁሳቁሶችን ለማድረስ የሚደረገው ጥረት በምርጫ ቦርድ ብቻ የሚሳካ እንዳልሆነና የተለያዩ ተቋማትን ድጋፍ እና ትብብር እንደሚፈልግም ገልጸዋል፡፡

በምርጫ ቦርዱ አቅም መሰረት እስከሁን በ673 ቦታዎች ላይ የምርጫ ቁሳቁሶችን ማድረስ መቻሉን የገለፁት ወይዘሪት ብርቱኳን ፣ በቀጣይ ሳምንታት ደግሞ በ50 ሺህ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ለማድረስ ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

ከእጩዎች ምዝገባ ጋር ተያይዞ ከአማራ ፣ደቡብ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ውጭ በሌሎች ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የእጩዎች ምዝገባ መጀመሩንም ገልጸዋል፤ በቅርብ ቀናት ደግሞ አራቱ ክልሎችም እንደሚጀምሩም ተመልክቷል፡፡

የምርጫ ቁሳቁስ ማጓጓዣ ችግር አፋጣኝ እልባት ካላገኘ አገር አቀፉን የምርጫ ሂደት ሊያስተጓጉል ይችላል ሲል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።ቦርዱ በመተከል በሁሉም ወረዳዎች የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤቶች መክፈቱንም አስታውቋል።የኢትዮጰያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች ምዝገባ መረጃ፣በምርጫ ቁሳቁስ ስርጭትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ዛሬ ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።
በዚሁ ጊዜ በዕጩዎች ምዝገባ፣የመራጮች ምዝገባ መረጃ፣ የምርጫ ጣቢያ ዝግጅትና የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭትን በተመለከተ ያለውን ዝግጅት ለፓርቲዎቹ ገለጻ አድርጓል።የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሰፊ አገርና ህዝብ ነገር ግን የመንገድ መሰረት ልማት ውስንነት ያለበት አገር ላይ ምርጫን በአግባቡ ለማካሄድ መንግስት ከፍተኛ እገዛ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ሁሉንም የአገሪቱ አካባቢ ሊሸፍን የሚችል የትራንስፖርት አቅም ያለው መከላከያ ሰራዊት መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ በትግራይ በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ በተፈጠረው ጫና እገዛው መስተጓጎሉን ተናግረዋል።የማጓጓዣ ችግሩ አፋጣኝ እልባት ካልተሰጠው የምርጫ ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያስተጓጉል ይችላል በማለት ተናግረዋል ሰብሳቢዋ።
ቦርዱ በመላ አገሪቷ 663 የምርጫ ክልሎችን ከፍቶ የምርጫ ቁሳቁሶችን እያጓጓዘ ሲሆን በቀጣይም ለ50 ሺህ ምርጫ ጣቢያዎች እንደሚያሰራጭ አስታውቋል።ማጓጓዣው በየአካባቢው እንዳለው መሰረተ ልማት በየብስ፣ በጀልባ እንዲሁም በበቅሎና ፈረስ ጭምር ሊሆን እንደሚችልም ነው ያመለከቱት።
ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ የክልል አመራሮች የመጓጓዣ ችግሩን ለመፍታት ከቦርዱ ጋር መተባበር እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
ወይዘሪት ብርቱካን በመተከል ዞን አስቸጋሪ የጸጥታ ሁኔታ የነበረ ቢሆንም ከጸጥታ ግብረ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት በሁሉም የመተከል ወረዳዎች ላይ የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤት መከፈቱን ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ ቦርዱ ከመጓጓዣ ጋር ተያይዞ ያጋጠመው ችግር ከክልል አመራሮች ጋር በመነጋገር እንደሚፈታ ገልጸዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዥው ፓርቲ አባሎቻችንን ያለአግባብ አስሯል፣ ቢሯችንን ዘግቷል ብለው ላቀረቡት አቤቱት ዶክተር አለሙ በሰጡት ምላሽ ”ምርጫ እናሳምራለን ተብሎ በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ተከሳሾችን ለማስመለጥ የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
ይሁንና ሚዛን በማይደፋ ጥፋት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና ደጋፊዎች ላይ የሚደርስ ጥቃት ካለ ፓርቲያቸው ጉዳዩን አጣርቶ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል።

EBC