ብልጽግና ልክ ኢሕአዴግ ደጋግሞ ሲያደርገው እንደነበረው ሰማንያም ዘጠናም በመቶ አሸነፍኩ የሚል ከሆነ እንደተሸነፈ ይቆጠራል።

በምርጫው አሸንፎ መሸነፍ ወይስ ተሸንፎ ማሸነፍ? – (ዳዊት ዋበላ)

በዘመነ ሕወሓት/ኢሕአዴግ 5 ብሔራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በአምስቱም ኢሕአዴግ አሸነፍኩ እያለ፣ ነገር ግን በየጊዜ ከሕዝብ ልብ ውስጥ እየወጣና ቅቡልነቱን እያጣ ነበር የሄደው። በምርጫ 2007 መቶ በመቶ አሸነፍኩ ባለ ማግስት ከሕዝቡ ልብ ውስጥ ተጠራርጎ ስለወጣ ከምርጫው ማግስት ጀምሮ በተቃውሞ ሲናጥ ከርሞ በመጨረሻም ጥልቅ ተሐድሶ ውስጥ ገብቻለሁ፣ ጊዜ ስጡኝ እያለ ቢማፀንም የሚሆን አልሆነም። በምርጫ “አሸንፎ” ተሸነፈ!

እንደሚታየው የብልጽግና አካሄድም ትክክል አይደለም። ብልጽግና በመጪው ምርጫ ልክ እንደ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የመወዳደሪያ ሜዳውን ኢፍትሐዊ በማድረግ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ሕዝብ እንዳያደራጁና እንዳይቀሰቅሱ እንቅፋት በመፍጠር፣ ፖለቲከኞችንና ሌሎች የፖለቲካ ተዋናዮችን በማዋከብ፣ በማሰርና በመግደል፤ በጥቅሉ ፍርሃት በማንገሥ አሸነፍኩ የሚል ከሆነ እንደተሸነፈ ግልጽ ነው። እንዲህ ዓይነት የጨረባ ምርጫ እያደረጉ መቀጠል ይቻላል፤ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ለ27 ዓመታት እንደቆየው። ሆኖም የሕግና የሞራል ተቀባይነት ማግኘት አይቻልም። ልክ ደርግና ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሲያደርጉት እንደነበረው ሕዝብ ቀስቅሶ ሰልፍ ማስወጣት ይቻላል። ብዙ ሰው እንዲመርጥ ማድረግም ቀላል ነው። በአፍሪካ የመራጭ ቁጥር (voter turnout) አጀንዳ አይደለም፤ በትዕዛዝና በጥቅማ ጥቅም ስለሚያዝ። ሆኖም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ባለመሆኑ ውጤቱ ከንቱ ነው።

መማር ለፈለገ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ታሪክ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው። የብልጽግና አመራሮች ከኖሩበትና ትክክል አልነበረም ብለው ኂስ ካደረጉት የኢሕአዴግ አስተሳሰብ ራሳቸውን በብዙ ኪሎ ሜትሮች ቢያርቁ ለራሳቸውም ለአገራቸውም ትልቅ ታሪክ ይሠራሉ። ይህን ታሪካዊ ዕድል ካባከኑት ግን ከቀድሞዎቹ ኢሕአዴግ አመራሮች የበለጠ ተጠያቂዎች እንደሚሆኑ አያጠያይቅም።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለው የዘውግ፣ የሃይማኖት እና/ወይም አመለካከት ልዩነት አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግሥት ሊመሠርት የሚችልበትን ዕድል የሚዘጋ ነው። ቢያንስ ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘትን በጣም አስቸጋሪ የሚያደርግ ነው። በእንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ብልጽግና ልክ ኢሕአዴግ ደጋግሞ ሲያደርገው እንደነበረው ሰማንያም ዘጠናም በመቶ አሸነፍኩ የሚል ከሆነ እንደተሸነፈ ይቆጠራል። “አሸንፎ” ተሸነፈ ማለት ነው።

(ዳዊት ዋበላ)
ሲራራ-ሐሳብ!

May be an image of one or more people and text that says 'ብልጽግና ፓርቲ Prosperity Party'