ብስለት የጎደለው ፖለቲካ ውድቀትን ያመጣል – የሰለጠነ ፖለቲካ ያስፈልገናል።

ምንሊክ ሳልሳዊ : ብስለት የጎደለው ፖለቲካ ውድቀትን ያመጣል። የፖለቲካ ድርጅቶች ካድሬዎቻቸውን አብስለው በሕዝብ ትግል የተገኘውን የለውጥ ሒደት ሊጠቀሙበት ይገባል። የሰለጠነ ፖለቲካ ያስፈልገናል። መልካም ጅማሮውን ለውጥ አድርገን ልንተረጉመው የምንችለው በወሬና በዜና መረጃ ቀውስ በመፍጠር ሳይሆን ፖለቲካ በመስራት ነው።

ኢሕአዴግ የማይታመን ድርጅት ነው። ከዚያን ጎን ለጎን በጎጥና በዘር ላይ የተደራጁ ድርጅቶች ጠባብነታቸውን በሕዝብ ላይ ለመጫንና የመከነ ዘረኛ ትውልድ ለመፍጠር ዛሬም እየደከሙ ነው። ይህን ድካም ደግሞ ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ጎጥና ዘር አይተነው ምንም ለውጥ አላመጣም ፤ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም አንድነትና ሰርቶ መብላት መሆኑን ፖለቲከኞች ከተረዱትና ካድሬዎቻቸውን አብስለው ማውጣት ከቻሉ ዘረኞችን የማያደቁበት ምክንያት የለም። በኢሕአዴግ ውስጥ የተለወጠ ነገር ቢኖር ጥቂት የለውጥ ሃይሎች መፈጠር ብቻ ስለሆነ ኢሕአዴግን ከሚከተለው የፖለቲካ ባሕርይ አንጻር ልንመዝነው ልንገምተው ይገባል።

የፖለቲካ ድርጅቶች በዲፕሬዥንና ስትረስ የሚሰቃዩ ቦዘኔዎችን ማስወገድ አለባቸው። የፖለቲካ እውቀት ያላቸውንና የተሻለ ሃገራዊ ራእይ የሰነቁ ካድሬዎችን ሊያፈሩ ይገባል። ካልሆነ እየተወዛወዙ ሽሙጥና ዘለፋ የኢሕ አዴግ ካድሬዎችንም ከጥቅም ውጪ አድርጓቸዋል። በሃገር ውስጥ ለሚዘረጉ ኔትወርኮች የተሻለ ስራ የሚሰሩ ካድሬዎችን መፍጠር ካልተቻለ ነባሩንም ኔትወርክ ለአደጋ ማጋለጥ ይሆናል።

ፖለቲካ ሲደራጅ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ሊሰሩና ሊያሰሩ የጠላትን ወገን ሐሳብ አስቀይረው ወደ ትግሉ የሚቀላቅሉ የሰከኑ ካድሬዎች ያስፈልጋሉ። ብስለት የጎደለው ፖለቲካ ውድቀትን ያመጣል። ከተለያዩ ቦታዎች ተሁኖ በስድብ ማምታታት ስልጣኔ አይደለም። ፖለቲካ ስድብና ዘለፋ የተዋኻደው እለት እንደሰይጠነ ይቆጠራል። የሰለጠነ ፖለቲካ ለማራመድ የሚረዳው በጋራ ተመካክሮ ሃሳብን በማዳበር ብቻና ብቻ ነው። የሰለጠነ ፖለቲካ ያስፈልገናል። ምንሊክ ሳልሳዊ