ዶክተር አቢይ አሕመድ የብልጽግና ፓርቲ ማኒፌስቶ እና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ አደረጉ።

“የብልጽግና ማንፌስቶ ኮንትራት ሳይሆን ቃል ኪዳን ነው፤ የፖሊሲ ሰነዱም ድርሰት አይደለም”
– የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐብይ አህመድ
May be an image of 1 person(ኢ.ፕ.ድ)“የብልጽግና ማንፌስቶ ኮንትራት ሳይሆን ቃል ኪዳን ነው፤ የፖሊሲ ሰነዱም ድርሰት አይደለም፤” ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐብይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ዶክተር ዐብይ የፓርቲው የማኑፌስቶና የመወዳደሪያ ምልክት ይፋ የማድረጊያ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የብልጽግና ማንፌስቶ በህዝቡ እና በፓርቲው መካከል የተገባ ቃል ኪዳን እንጂ ኮንትራት አይደለም፤ ሰነዱም ቃልኪዳኑን መፈጸሚያ ሰነድ እንጂ ድርሰት አይደለም ብለዋል፡፡
ዶክተር ዐብይ በመልዕክታቸው “በእኛና በህዝባችን መካከል የምንገባው ኮንትራት ሳይሆን፤ በእኛ እና በህዝባችን መካከል የምንገባው ቃልኪዳን ነው፡፡ ምክንያቱም ኮንትራት በሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ስለሚመሰረት፤ አንዱ ማድረግ ሲያቅተው የሚፈርስ ነው፡፡ ቃል ኪዳን ግን በሁለትዮሽ ቁርጠኝነት ላይ የሚመሰረት እንደመሆኑ፤ አንዱ ቢደክም ሌላው እያገዘው የሚዘልቅ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው” ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይህ ቃልኪዳን የያንዳንዱን የብልጽግና አባል በፍጹም ቁርጠኝነት ራሱን መስጠትና ማገልገል ላይ የሚመሰረት፤ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ከህዝባችን ጋር በመተባበር ለትውልድ የምናስረክብበት ነው ብለዋል፡፡
“ይህ ሰነድ ድርሰት አይደለም፤ ብዙዎች ድርሰት እያዘጋጁ ነው፡፡ ሆኖም ፖሊሲ ድርሰት መሆን አይችልም፤ ማንፌስቶም ድርሰት አይሆንም፡፡ ለአንድ አመት የሚዘጋጅ ጉዳይም አይደለም፡፡ በሰፊ የመረጃ ማሰባሰብ፣ መተንተንና ከዛ ተምሮ ለነገ የሚሆን አበይት ጉዳዮችን አካቶ ለገባነው ቃል ኪዳን የምንሄድበት ሰነድ ነው፡፡ በመሆኑም ከወርና ከሁለት ወር በኋላ እኔ ፖሊሲ አለኝ ማለት ብቻውን ትርጉም አይኖረውም፡፡ እናም ፖሊሲ ድርሰት ሳይሆን ቃል ኪዳንን መወጫ ሰነድ ሆኖ መዘጋጀት ይኖርበታል” ነው ያሉት፡፡
ብልጽግና የሚናገረውን የሚያደርግ፤ የሚጀምረውን የሚጨርስ ነው፡፡ ይሄንንም ባለፉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በተግባር ያሳየ፤ ቃሉንም የፈጸመ ነው ያሉት ዶ/ር አብይ፤ የህዳሴ ግዱቡ ላይ የተፈጸመውም ይሄው እንደሆነና ህዝቡም ብርሃን ይፈልጋልና ብርሃን እንዲያይ የሚያስችል መልካም ግስጋሴውን አሳይተነዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ብልጽግና የመደመር መንገድን የፈጠረ እና የብዙዎች የሆነውን የርዕዮተ ዓለም ስብራት መጠገን የቻለ ፓርቲ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የአገሪቱን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም በርካታ ውስብስብ ችግሮች ማቃለል የቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ የሚያፈርሳት ይፈርሳል እንጂ ባልነው መሰረት ሊያፈርሷት የሚሹትን ለመሸከም ዝግጁ እንዳልሆንም በተግባር ማሳየት ችለናልም ነው ያሉት፡፡
ተረኛና ተረኝነት ከሚል አስተሳሰብ በመውጣትም ከሁሉም ለሁሉም በመቆም እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡በቀጣዩ ምርጫ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ የሚያደርግ እንዲሆን እንደሚሰራ ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ በመልዕክታቸው የተናገሩት፡፡
May be an image of 1 person and text