ራሱ ቀይ ባህር የኢትዮጲያ የተፈጥሮ ወሰን ሆኖ ኖሯል ይኖራልም – ራስ አሉላ አባነጋ

የራስ አሉላ የዶጋሊ ድል  – 134ኛ ዓመት መታሠቢያ
“…እኔ የሮማ ጠቅላይ ገዥ ሆኜ ስሔድ ያን ግዜ ጣሊያኖች ሰሐጢ ድረስ ሊመጡ ይችላሉ። አንዴ ክንዴን አሳይቻቸዋለሁ እንደገና ከመጡም እደግማቸዋለሁ! ራሱ ቀይ ባህር የኢትዮጲያ የተፈጥሮ ወሰን ሆኖ ኖሯል ይኖራልም…” ራስ አሉላ አባነጋ።

ቱርኮች ምጽዋን መያዛቸውን የሰሙት አጼ ዮሐንስ የጦር አዛዣቸው ለነበሩት ራስ አሉላ “እስክመጣ ድረስ ተጨማሪ ቦታ እንዳይዙ ነቅታችሁ ጠብቁ” ብለው መልዕክት ላኩ ራስ አሉላ ግን “ለጌታ ድግስ እንጂ ጦር አያቆዩትም” ብለው ቱርኮችን ተዋግተው ድል አረጉ፡፡
የራስ አሉላን እጅ ያልቀመሰችው ኢጣሊያም በተራዋ ከ 3 ዓመት በኋላ መጥታ ምፅዋና አካባቢው ላይ ጦሯን አሰፈረች ራስ አሉላም በድጋሚ ኢጣሊያን ድል አደረጉ፡፡
በዚህ ጊዜ የኢጣሊያ መንግስት በሽንፈቱ በጣም ተበሳጨ ለሁለተኛም ጊዜ ሦስት ክፍል ጦር ይዞ በመምጣት ጥር 17 ቀን 1879 ዓ/ም ዶጋሊ በሚባል ቦታ ከራስ አሉላ ጋር ውጊያ አደረገ።
በጦርነቱም የኢጣሊያ ጦር በትምህርት ካገኘው የጦር መላ ይልቅ ራስ አሉላ በተፈጥሮ ያገኙት ኢትዮጵያዊ ወኔና የጦር ዕቅድ ይበልጥ ነበርና የኢጣሊያን 500 ወታደሮች በመፍጀት ራስ አሉላ ታላቅ ድል አደረጉ፡፡ይሄ ድል በኢጣሊያ በተሰማ ጊዜ ታላቅ ሽብርን ፈጠረ፡፡በጎዳናዎችና በመስሪያ ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞን አስከተለ፡፡
ሰሐጢ ላይ ግብፆች በአሉላ ድባቅ ከተመቱ በኋላ ግብፅ (ከመጋረጃ ጀርባ እንግሊዝ) ግዛቴ ነው በማለት የያዘቻቸው ወረዳዎች ላይ የኢትዮጲያ የበላይነትና የአሉላም ክንደ ብርቱነት፣ የአፄ ዮሐንስንም ግልፅ አላማ ማለትም ጎሳ ከረን ምፅዋ የተባሉ ወረዳዎችን ወደ ኢትዮጲያ የማስመለስ አለማ እያረጋገጠው ሲሄድ በሱዳን በኩል መሀዲስቶች የአሉላን ስልት በመከተል በሀገራቸው ላይ የነበሩት ግብፆች ላይ ክንዳቸውን አነሱ።
ይህም የግብፃውያን ወታደሮችን የበላይነት እያገለለው መሄዱ እንግሊዞች ላይ ስጋት በመፍጠሩ ቀድመው ዘግተውት የነበረውን የዮሐንስን በር መክፈት አስፈላጊ እንደሆነ አምነውበት ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በሐምሌ 17 ቀን 1878 ዓ.ም ውል ፈፀሙ። በውሉም መሰረት ቀደም ብለው በእንግሊዝ ስር የነበሩ የኢትዮጲያ ግዛቶች በዮስ… ስንሐት… የተባሉ ቦታዎችን ጨምሮ ለንጉሠ ነገሥቱ ተመላሽ እንዲሆኑ ተስማሙ።
ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስም ሆኑ የመሳዋ (ኤርትራ) አስተዳዳሪ የነበሩት ራስ አሉላ ለውሉ ታማኝ የነበሩ ቢሆንም የውሉ ዘመን ማብቂያ በተቃረበበት ግዜ እንግሊዝ በቦታው የኢጣሊያንን ወታደሮች እንዲሰፍሩ አደረገች። ኢጣሊያም በግዜው የነበረውን የተወጠረ ግዜ በመጠቀም ምፅዋ ድረስ ገፍታ ገባች።
በወቅቱ ራስ አሉላ አባነጋ ከመሀዲስቶች ጋር ኩፊት በተባለ ቦታ ጦርነት ገጥመው ነበርና በድል ከተመለሱ በኋላ ለኢጣሊያው ጀነራል የያዛቸውን ቦታዎች እንዲለቅ ካልሆነ ወዳጅነቱ እንደሚያበቃ ገልፀው ደብዳቤ ላኩለት። ጀነራሉ ግን ወታደሮቹ የአካባቢውን ሰላም የሚጠብቁ በመሆኑ ከቦታው እንደማይለቁ ፃፈላቸው።ይህም የጦርነቱን አይቀሬነት አረጋገጠው።
በዶጋሊ በተደረገው ጦርነት የኢጣሊያውን 500 እግረኛ ጦር የመራው ቶማስ ዲ.ክርስቶፈሪ ሲሆን የኢትየጲያን 7000 እግረኛ ጦር የተመራው በራስ አሉላ አባነጋ ነበር። በጦርነቱ በኢጣሊያ በኩል ተሰልፈው ከነበሩት ወታደሮች 420 የሚሆኑት የተገደሉ ሲሆን የተቀሩት 80ዎቹ ቆስለው ተማርከዋል።
ከዶጋሊው ድል በኋላ ጣሊያን ቀርቶ መላው አውሮፓ በፍርሃት ንዷል።ይህንንም ለማረጋጋት በኢጣሊያ ሮም ከተማ ውስጥ “Termini” ከሚባል ባቡር ጣቢያ ፊት ለፊት ባለ “piazza dei cinquecento’ በሚባል ትልቅ አደባባይ ላይ በዶጋሊ ጦርነት ለሞቱ 500 የኢጣሊያ ወታደሮች ሰኔ 5 ቀን 1887 እ.ኤ.አ የመታሰቢያ ሐውልት ቆመላቸው፡፡ራስ አሉላ ደግሞ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ሐውልታቸውን ሰርተው ጀግንነታቸው በውጪ ሀገር ዜጎች ሳይቀረ አሁንም ድረስ እንደተተረከ ቀጠለ፡፡
 –
የዶጋሊው ድል የኢትዮጲያን ስም በዓለም እንዲነሳ ያደረገ ሲሆን ለአድዋው ጦርነት መነሻ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሆናል። ከዶጋሊ ድል በኋላ ፀረ _ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
አሉላ አባ ነጋ የደጋ ላይ ኮሶ፤
በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተቀምሶ።
ጣልያን ሰሐጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ፤
አንገብግቦ ቆላው አሉላ አባ ነጋ።
እኛስ ስለ ኢትዮጵያ የተዋደቁት አባቶች አባቶቻችን ናቸው። በሥራቸው እንኮራለን። በመንፈሳቸው እንኖራለን። ለአደራቸው እንታመናለን። “እናንተ ማን ናችሁ?” ብትሉን “ልጆቻቸው” እንላለን። አፍሪቃዊው ጄነራል። የዶጋሊው ድል ባለውለታ። የእናት ሀገር መልካም ፍሬ። ራስ አሉላ አባ ነጋ። የወንዶች ራስ። እንኳን ለዶጋሊው ድል መታሰቢያ አደረሳችሁ።
የካቲት 8 የታላቁ ጀግና እረፍት እለት !
በኩፊት፣ በዶጋሊ፣ በጉንደት፣ በጉርዓ፣ በሰሀጢ፣ በመተማ፣ በዓድዋ … ከወራሪዎች ጋር ተፋልመው አንፀባራቂ ድሎችን ያስመዘገቡት ጀግናው የኢትዮጵያ ልጅ እና ባለውለታችን፣ ራስ አሉላ እንግዳ (አሉላ አባ ነጋ) ያረፉት ከዛሬ 123 ዓመታት በፊት (የካቲት 8 ቀን 1889 ዓ.ም) ነበር፡፡
ጀግናው ራስ አሉላ ካሸነፋቸው አውደ ውጊያዎች መካከል
፩ /ከኦቶማን ግብፅ -ጉንደት ላይ 1875 እኤአ
፪ /ጉራዕ – መጋቢት 1876 እኤአ
፫ /አይለት- 1887 እኤአ
፬ /ሰሃጢ -1880 እኤአ
፭ /ከሱዳን መሀዲስት -ኩፊት 1885 እኤአ
፮ /ጋላባት /መተማ – 1889 እኤአ
፯ /ከጣሊያን -ሰሀጢ 1887 እኤአ
፰ /ዶጋሊ-1887 እኤአ
፱ /ዐምባላጄ – 1889 እኤአ
፲ /መቐለና ዓድዋ -1896 እኤአ
ራስ አሉላ ዘመኑን ሙሉ ለኢትዮጵያ ሲዋደቅ የኖረ ጀግና ነው!
ዘላለማዊ ክብር ለራስ አሉላ እንግዳ (አባነጋ) !!!