በሃላባ ታቦታት መስጂዱ አቅራቢያ ሲደርሱ ድንጋይ መወርወሩ ተረጋግጧል

ትላንት በሀላባ የተፈጠረው ምንድነው?

በትላንትናው ዕለት በሀላባ ከተማ የጥምቀት በዓል ተከብሮ ታቦታቱ ከባህር ጥምቀት በመንሳት ወደየደብራቸው በሚጓዙበት ወቅት ኑር መስጊድ አቅራቢያ ሲደርሱ የድንጋይ ውርወራ በመጀመሩ ታቦታት ወደደብራቸው ሳይደርሱ ጉዟቸውን አቋርጠው በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንዲገቡ ተደርጎ እንደነበር ተገልጿል።

በዚህም በርካታ ምዕመናን ቀላልና ከባድ አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን በግፊያና በመረጋገጥም አቅመ ድካሞችም ሳይጎዱ እንዳልቀረ ተነግሯል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በሀላባ ቁሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓልም ነው የተባለው።

የሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃሩና አህመድ ”ሁለቱንም ሃይማኖት የማይወክል ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ነው” ያሉ ሲሆን ይህ ድርጊት የፈፀሙ ፀረ-ሰላም የሆኑ አካላትን ከተማ አስተዳደሩ ብርቱ ክትትል በማድረግ ለህግ እንደሚያቀርባቸው ገልፀዋል።

የችግሩን መከሰት ተከትሎ የከተማውን ፖሊስ ተክቶ የሰላም ማስከበሩን ስራ የደቡብ ክልል ልዩ ኃይልና የፌድራል ፖሊስ አባላት ተቀናጅተው ግጭቱን በቁጥጥር ስር አውለው ከቀኑ አሥር ሰዓት በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የቆዩት ታቦታቱ ወደየደብራቸው ተመልሰው እንዲገቡ ተድርጓል።
(EotcWestArsiDiocese, HalabaTV)