የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱ ከሀገራቱ ወዳጅነት ጋር የሚጻረር ነው – ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

  • ከጥቅምት 30 ጀምሮ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱ ተገለጸ
  • ም/ጠ/ሚ እና የውጭ/ጉ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን “ይህ ድርጊት ከሀገራቱ ወዳጅነት ጋር የሚጻረር ነው” ብለዋል
አል-ዐይን

የሱዳን ጦር በፈጸመው ጥቃት በርካታ ንጹሀን መገደላቸውን እና ንብረት መውደሙን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል

በካርቱም እየተካሔደ በሚገኘው ሁለተኛው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር የጋራ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ውይይት ላይ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተለያዩ የሁለትዮሽ ጉዳዮችን የተመለከተ ንግግር አድርገዋል፡፡

ከጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ በተደራጀ መልኩ ጥቃት እየፈጸሙ ስለመሆናቸው አቶ ደመቀ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡ ይህ ማለት በትግራይ ክልል የተፈጠረው ቀውስ ሳምንት እንኳን ሳይሞላው ነው የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመረው፡፡

አቶ ደመቀ በንግግራቸው “ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም የሱዳን ጦር የተደራጁ ጥቃቶችን እየፈጸመ መሆኑን እየተመለከትን ነው” ብለዋል፡፡ በዚህም “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶች ተዘርፈዋል ፤ ካምፖቻቸው ወድመዋል እንዲሁም የራሳቸውን የእርሻ ምርት እንዳያጭዱ ተደርገዋል” ያሉት አቶ ደመቀ በርካታ ንጹሀን ስለመገደላቸው እና ስለመቁሰላቸውም ገልጸዋል፡፡ እናም በድንበር አከባቢዎች የተከሰተው የቅርብ ጊዜ ክስተት የኢትዮጵያን መንግስት ክፉኛ እንዳሳሰበው ነው በንግግራቸው ያካተቱት፡፡ ም/ጠ/ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ይህ ሁኔታ በሰሜን ዳግልሽ ተራራ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ባለበት ለማቆየት የደረስናቸውን ስምምነቶች አደጋ ላይ እየጣለ ነው” በማለት ስጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡

“በድንበር አካባቢ ባሉ ማህበረሰቦች መካከል መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር ፣ የድንበር ጉዳዮችን ለመፍታት እና ሰላምን እና ደህንነትን ለማስጠበቅ” ባለፈው ግንቦት ወር አዲስ አበባ ላይ ፍሬያማ ውይይት ተደርጎ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና “በቅርብ ጊዜ የተመለከትነው ሁኔታ በሁለታችን ሀገራት መካከል ካለው መልካም ግንኙነት ጋር የሚጻረር ነው” ሲሉም የተፈጠረውን ድርጊት አውግዘዋል፡፡

ስለሆነም ከዚህ ቀደም የነበሩትን አሰራሮች በመተግበር መፍትሄ መፈለግ ለጋራ የድንበር ጉዳዮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ብቸኛው መንገድ መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡ አቶ ደመቀ አክለውም “አላስፈላጊ ውጥረትን መፍጠር በድንበር አከባቢ ያለውን ሁኔታ ከማባባስና ትርጉም የለሽ ስጋት ከመፍጠር ባሻገር በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦቻችንን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያደናቅፍ እንደሆነ እናምናለን” ብለዋል፡፡

“ሁልጊዜም የኢትዮጵያ እና የሱዳን ግንኙነት ምልክት በሆነው ወንድማዊ ትብብር እና ቁርጠኝነት” ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡

አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ፣ በሁለትዮሽ ፣ በቀጣናዊ እና ዓለማቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ከሱዳን መንግስት ጋር በቅርበት ለመስራት ጽኑ አቋም እንዳለውም አረጋግጠዋል፡፡

የሱዳን መንግሥት በትግራይ ክልል በነበረው የሕግ ማስከበር ሂደት ድጋፍ ማድረጉን በመግለጽ ለዚህም አቶ ደመቀ መኮንን ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አል-ዐይን