የሕወሓት አባላት የሆኑ የትራንስ ኢትዮጵያ ሹፌሮች በጅቡቲ 183 ከባድ ተሽከርካሪዎችን አግተዋል ተባለ

Image may contain: 1 person, sitting and indoorየኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተለያዩ የወንጀል ተግባር ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል በተጠረጠሩ ድርጅቶች ላይ የንብረት እገዳ እንዲጣል ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ የታገዱትን ድርጅቶች ንብረቶች ባሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ ለማድረግ ተገቢውን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ከእነኚህ ከታገዱት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የትራንስ ኢትዮጵያ ንብረት የሆኑ ለስራ ወደ ጂቡቲ የተጓዙ እና ወደ ሀገር ቤት ሳይመለሱ የቀሩ 179 (አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ) የደረቅ ጭነት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች እና አራት የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ (ቦቴ) አሁን ላይ በጂቡቲ ሀገር ይገኛሉ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እና የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ ስለሚቻልበት ሁኔታ ጂቡቲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ከጂቡቲ መንግስት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የዐቃቤ ህግ እና የፖሊስ ተቋማት የበላይ አመራሮች ጋር የተሳካ ውይይት አድርጓል፡፡
Image may contain: 1 person, sitting, living room, table and indoorእኚህ ተሽከርካሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር ቤት እስከሚመለሱ ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት ከጂቡቲ መንግስት ጋር በመተባበር ጠንካራ ጥበቃ እያደረገላቸው መሆኑን በውይይቱ የተሳተፉት የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በወንጀል የተገኙ ሀብቶች ማስመለስ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አለም አንተ አግደው ገልጸዋል፡፡
እነኚህን ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ለመመለስ የተደረገው ጥረት ከህዝብ አገልጋይነት ስሜት በተቃረነ ሁኔታ የህወዓት አባል እና የቀድሞ ታጋይ የነበሩት የተሸከርካሪዎቹ ሾፌሮች ወይም አሽከርካሪዎች ተሸከርካሪዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆን ተልዕኮው እንዳይሳካ ጥረት ቢያደርጉም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ጂቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጂቡቲ መንግስት ጋር በጋራ በመሆን ተሸከርካሪዎቹን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ተገቢውን ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል፡፡