ህወሓት ጦርነት ለማድረግ የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና የለውም

“ጦርነት የለም፤ ህወሓት ጦርነት ለማድረግ የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና የለውም” አቶ ዛዲግ አብርሃ – BBC Amharic

አቶ ዛዲግ አብርሃ

በአሁኑ ጊዜ ትግራይ ውስጥ የሚካሄድ ጦርነት እንደሌለና እየተደረገ ያለው የህወሓት አመራሮችን በማደን በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃ እንደሆነ አቶ ዛዲግ አብረሃ ገለጹ።

የዲሞክራሲ ግንባታ ሚንስትሩ አቶ ዛዲግ አብርሃ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በክልሉ የተካሄደው ጦርነት ማብቃቱን ጠቁመው በዚህ ወቅት “ጦርነት የሚባል ነገር የለም። አሁን ጥቂት የሚባሉ የአሸባሪ ቡድን አባላትን እየተከታተሉ መያዝ ነው የቀረው” ሲሉ ገልጸዋል።

መንግሥት ሕግ የማስከበር ያለው ዘመቻ የፌደራል መከላከያ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን መቆጣጠሩን ተከትሎ ማብቃቱን ነገ ቅዳሜ አንድ ሳምንት የሚሞላው ሲሆን በመንግሥት ኃይሎች እየተፈለጉ ያሉት የህወሓት አመራሮች ግን ፍልሚያ ላይ እንደሆኑ እየተናገሩ ነው።

ቀደም ሲል የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እንደሁም የቡድኑ ከፍተኛ አመራር አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ትናንት ለትግራይ ቴሌቭዥን እንደገለጹት “ጦርነቱ አልተገባደደም። አይገባደድምም” ብለዋል።

ነገር ግን ሚኒስትሩ አቶ ዛዲግ አብረሃ እየተካሄደ ያለው ተፈላጊዎችን የመያዝ ተግባር መሆኑን አመልክተው፤ በአሁኑ ወቅት “ህወሓት ጦርነት ማድረግ የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና የለውም። ወታደር የለውም። ትልልቅ መሣሪያዎች የሉትም። የሕዝብ ድጋፍም የለውም” ብለዋል።

ከሳምንት በፊት በተደረጉ ውጊያዎች ዋና ዋና የትግራይ ከተሞች በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እጅ ውስጥ ከገቡ በኋላ የህወሓት አመራር መቀለን ጥሎ ቢወጣም ጦርነቱን እንደሚገፋበት ማስታወቁ ይታወሳል።

አቶ ጌታቸው ረዳም ሠራዊቱ መቀለን መቆጣጠሩን አረጋግጠው የሚቀር ነገር እንዳለ “መቀለ ገብተዋል። መቀለን ተቆጣጠሩ ማለት ግን አይደለም። መቀለን መቆጣጠር የሕዝብን መንፈስና ልቦና መግዛት ይጠይቃል” ሲሉም ተደምጠዋል።

የመቀለ ከተማን ለመያዝ በተካሄደ ዘመቻ ወቅት ከተዋጊዎች ውጪ ባሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አንድም ሰላማዊ ሰው አልተጎዳም” ማለታቸውን በተመለከተ ቢቢሲ አቶ ዛዲግ አብረሃን ጠይቆ ነበር።

በሰጡትም ምላሽ ጠቅላይ ሚንስትሩ እተካሄደ ስለነበረው ዘመቻ ትክክለኛ መረጃ እንዳላቸውና የአገሪቱ ሠራዊትና የጸጥታ አካላት በክልሉ ውስጥ በቅንጅት እንደሚሰሩ ጠቁመው “የሕግ ማስከበር ዘመቻው ስትራቴጂ ሲወጣ አንድም ስህተት ላለመሥራት ለይቶ በማትቃት [በሰርጂካል ኦፕሬሽን] ላይ የተመሠረተ ነው። ስለዚህ በእኛ በኩል የሲቪል ጉዳትን ሙሉ በሙሉ አስወግደናል” ብለዋል።

በመንግሥት በኩል በዚህ ዘመቻ ትግራይ ውስጥ ያለው ሕዝብ እንዲጎዳ እንዳልተፈለገ ጠቅሰው ለዚህም አስፈላጊው ጥንቃቄ እንደተደረገ ተናግረዋል። “ጸቡም የሕግ ማስከበር ዘመቻውም በህወሓት ላይ እንጂ በሕዝብ ላይ የሚካሄድ አይደለም” ሲሉም አክለዋል።

አቶ ዛዲግ በተጨማሪም፤ “በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት አልደረሰም ስንል በእኛ በኩል እንጂ በእነሱ [በህወሓት] በኩል ማለታችን አይደለም። ሰላማዊ ሰዎችን እንደ ከለላ [ጋሻ] በመጠቀም ሕይወታቸውን ለማቆየት ሞክረዋል። በዚያ ምክንያት የመጣ ጉዳት ሊሆን ይችላል” ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳትን በተመለከተ መረጃ እንደሌላቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ዋና ከተማዋ መቀለ በአሁኑ ጊዜ እየተረጋጋች በመምጣቷ በቀጣይ መረጃ ሊያገኙ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

የህወሓት አመራሮች ግን በዘመቻው ሂደት ከተዋጊዎች ውጪ ባሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን በመግለጽ በተደጋጋሚ መንግሥትን ሲከሱ ቆይተዋል።

በትግራይ ክልል ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ዕለት አንስቶ የስልክ እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ በመቆየቱ በክልሉ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አልተቻለም።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ትግራይ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ አራት የበጎ አድራጎት ሠራተኞች በግጭቱ ወቅት መገደላቸው ተዘግቧል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የዲፕሎማቲክና የሰብአዊ እርዳታ ድርጅት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በሁለት የተለያዩ የውጪ የተራድኦ ድርጅቶች ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ አራት ኢትዮጵያውያን የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኞች በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ተገድለዋል።

ስለዚህ ጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንዳለ በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ዛዲግ አብረሃ ፤ “አሁን ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም። ገና መረጃው እየተጠራ ነው ያለው። የስልክ አገልግሎትን እየመለስን፣ መንገዶችን እያስተካከልን ነው ያለነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በትግራይ ክልል ውስጥ የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁ ከተገለጸ በኋላ መንግሥት መረጋጋት ማስፈን፣ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባትና የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንዲቋቋሙ ማድረግ ዋነኛ ትኩረቱ ማድረጉን ገልጿል።

በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው ውዝግብ ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ መካረሩ ይታወሳል።

ይህንን የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ባለመቀበል በትግራይ ክልል የተካሄደው የተናጠል ምርጫ የፌደራል መንግሥቱን ተቀባይነት ካለማግኘቱ በተጨማሪ በአገሪቱ ምክር ቤቶች ሕገ ወጥ ተብሎ ውድቅ ተደርጓል።

የክልሉ ባለስልጣናትም በበኩላቸው ፌደራል መንግሥቱ በኮቪድ ሰበብ ምርጫን ማራዘሙ “ሕገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ ነው ስልጣኑን አራዝሟል” በማለት የፌደራሉን መንግሥት “ሕገወጥ” ብለው እውቅና መንፈጋቸው አይዘነጋም።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የክልሉን አስተዳዳሪዎች ሕገ መንግሥቱን በመጣስና ከሕግ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል በማለት የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል ክልል አስተዳደር ጋር የነበረውን የቀጥታ ግንኙነት አቋርጦ የበጀት ዕቀባ ጥሎ ነበር።

አለመግባባቱና መካሰሱ ያለማቋረጥ በቀጠለበት ሁኔታ ጥቅም 24/2013 ዓ.ም ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ክልል በነበሩት የሠሜን ዕዝ አባላት ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ካደረጉ በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት በህወሓት ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል።

ባለፈው ቅዳሜ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ሰር ከዋለች በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አሳውቀዋል።