የኅዳር ጽዮንና አክሱም ጽዮን ማርያም በመምህር ዘመድኩን በቀለ

የኅዳር ጽዮንና አክሱም ጽዮን ማርያም

በመምህር ዘመድኩን በቀለ

  በትግራይም ሆነ በኢትዮጵያ ተተክሎ ይመለክ ያስመልክ የነበረው ህወሓት የተባለ ዳጎን የተሰባበረበትና የደቀቀበትም ዕለት ነው። ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት። መዝ 87፥5

ዛሬ የኅዳር 21/2013 ዓም ነው። የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ሀገራችን መናገሻ ከተማ በነበረችው አክሱም ከተማ ውስጥ በምትገኘው” በርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን “ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ የሆነ ሃይማኖታዊ በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይፈጸማል።

የዛሬው የኅዳር ጽዮን ማርያም በዓል ስለ 8 ዓበይት ነገሮች ይከበራል 

፩፣ ታቦተ ጽዮን በምርኮ በሄደችበት በሀገረ ፍልስጤም ዳጎን የተባለን ስመ ጥር የአህዛብ ጣኦት አድቅቃ በድል የተመለሰችበት ዕለትን በማሰብ። 1ኛ ሳሙ 1-6።

፪፣ ታቦተ ጽዮን ንጉሥ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ቤተ መቅደስ በክብር የገባችበትን ዕለት በማሰብ። 1ኛ፣ ነገ 8፥ 1-66።

፫፣ ታቦተ ጽዮን በንግሥት ሳባ ልጅ በቀዳማዊ ምኒልክ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ምድር የገባችበትን ዕለት በማሰብ።

፬፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በአብርሀ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት መሆኗ የታወጀበት ዕለት በመሆኑ።

፭፣ በብሉይ ኪዳን መስዋዕተ ኦሪት/የእንስሳት ደም ከሚሰዋባት ሙኵራብ / ወደ ሀዲስ ኪዳን/ አማናዊው በግ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትበት /” ጽዮን ማርያም ተብላ ወደ ቤተ ክርስቲያንነት የተቀየረችበት ዕለት በመሆኑ።

፮፣ የቀደሙ ነብያት ስለ እመቤታችን በተለያየ ህብረ አምሳል ያዩበት፤ ለምሳሌ ነብዩ ዕዝራ በሃገር መንፈሳዊት፣ ሕዝቅኤል በተዘጋች ቤተመቅደስ፣ ዘካርያስ በተቅዋመ ወርቅ ወዘተ ያዩበትን ዕለት በማሰብ።

፯፣ በአረመኔዋ ዮዲት ጉዲት ከመፍረሱ በፊት፤ በሁለቱ ደጋግ ወንድማማች የኢትዮጵያ ነገሥታት በነበሩት በዘመነ አብርሀ ወአጽብሃ በወርቅና በዕንቁ የተሠራው ባለ አሥራ ሁለት ክፍሉ ቤተመቅደስ ሥራው ተጠናቅቆ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበትን ዕለት በማሰብ።

፰፣ በአረመኔዋ ዮዲት ጉዲት መነሳት ምክንያት ለ600 ዓመታት ያህል ወደ ዝዋይ ገዳም ተሰድዳ የነበረችው ታቦተ ጽዮን የስደት ዘመኗን ፈጽማ ወደ መንበረ ክብሯ አክሱም ጽዮን የተመለሰችበት ዕለት በመሆኑ፤ ይህንና ይህን በመሳሰሉ ምክንያቶች የህዳር ጽዮን በዓል በታላቅ ድምቀት ይከበራል ።

እኔም ከዚህ ታላቅ መንፈሳዊ በረከት ከሚታፈስበት ማዕድ ላይ ለመታደም ሳልችል ቀርቼ በአካል ብርቅም በሀሳቤ ግን እዚያው አክሱም ነኝ። ዘንድሮ ደግሞ የተለየ ነው። ታቦተ ጽዮን በውስጧ ከደጃፏ የነበረውን ህወሓት የተባለ የኢትዮጵያ ነቀርሳን በዓመታዊ ክብረ በዓሏ ዋዜማ ከመላው ትግራይም ሆነ ኢትዮጵያም አድቅቃና ሰባብራ  የጣለችበት ታሪካዊ ዕለት ነው። አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ከአማናዊቷ ታቦት አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት በረከቷን ያሳድርብን። አሜን።

ሻሎም !  ሰላም !

ዘመድኩን በቀለ ነኝ።

መጀመሪያወ ኅዳር 20/2009 ዓም

በመቀጠል ኅዳር 20/2012 ዓም በፌስቡክ ተለጠፈ።

ለሦስተኛ ጊዜ ኅዳር 21/2013 ዓም መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎለት በድጋሚ በቴሌግራም ቻናሌ፦

ከራየን ወንዝ ማዶ ተለጠፈ።