ትግራይ ተዋጊ ጀት መቶ የመጣል አቅም ባለቤት አይደለችም – የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት

“የጥፋት ቡድኑን የተለዩ ኢላማዎች በተገቢው ጊዜና ወቅት እንመታለን ” – ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ተሰማ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር …. አጥፊው ቡድን በትግራይ አየር ሃይል አማካኝነት የኢፌዲሪ አየር ኃይልን ጀት መትቼ ጥያለሁ ማለቱን የገለጹት ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ትግራይ የእራሷ አየር ሃይል የላትም ፤የኢፌዲሪን ተዋጊ ጀት መቶ የመጣል አቅም ባለቤት አይደለችም ብለዋል።
(ኢ ፕ ድ) የህወሀት የጥፋት ቡድንን የለዩ ኢላማዎችን በተገቢው ጊዜና ወቅት እንደሚመቱ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ተሰማ አስታወቁ ። የወንጀለኛው ቡድን ተይዞ ለህግ እንደሚቀርብ ገለጹ።
ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ተሰማ ትናንት ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት ፣የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እና አየር ኃይል በአጥፊው ህወሃት ቡድን ላይ እያደረሰ የሚገኘው ጥቃት ተጠናክሮ ይቀጥላል። የጥፋት ቡድኑ ያለባቸው ኢላማዎችም በተገቢው ጊዜና ወቅት ይመታሉ። የወንጀለኛው ቡድንም ተይዞ ለህግ ይቀርባል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል በየትኛውም አካባቢ የገበያ ቦታዎችን፣ ህዝብ የተሰበሰበባቸውን ቦታዎች እና ከተሞች አካባቢ በትንቃቄ እንደሚንቀሳቀስ ያመለከቱት ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ፣ አየር ኃይልም ሆነ የመከላከያ ሰራዊቱ ኢላማው በጽንፈኛው ቡድን ህወሃት ላይ ብቻ ነው ብለዋል።
የአየር ኃይል ጀቶች በትግራይ ክልል የተሰጣቸውን ኢላማ ብቻ ነጥለው በመምታት ግዳጃቸውን በብቃት እየፈጸሙ ይገኛል። በዚህም አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ላይ እንደሆኑ አስታውቀዋል።
የአጥፊው ቡድን ህወሃት ቀደም ብሎ በትግራይ ክልል ማንኛውም አውሮፕላን መንቀሳቀስ አይችልም፤ ከገባም መተን እንጥላለን የሚል ፉከራ አሰምቶ እንደነበር ያስታወሱት ሜጀር ጄኔራል መሃመድ፤ ከዚህ ንግግር በኋላ በተደጋጋሚ የኢፌዲሪ አየር ሃይል ጀቶች በሚፈለጉበት ሰዓት ግዳጃቸውን ፈጽመው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
የአጥፊው ቡድን ህወሃት ቀድሞ የተናገረው ቅጥፈት አሳፍሮት ህዝብን ለማደናገር የተፈበረከ ወሬ በመንዛት ላይ መሆኑን አመልክተው ፣ ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በትግራይ ሚዲያ የኢፌዲሪ አየር ሃይልን መትቼ ጥያለሁ የሚል የተለመደ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ አካል እንደሆነ አስታውቀዋል።
አጥፊው ቡድን በትግራይ አየር ሃይል አማካኝነት የኢፌዲሪ አየር ኃይልን ጀት መትቼ ጥያለሁ ማለቱን የገለጹት ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ትግራይ የእራሷ አየር ሃይል የላትም ፤የኢፌዲሪን ተዋጊ ጀት መቶ የመጣል አቅም ባለቤት አይደለችም ብለዋል።
የአጥፊው ቡድን የሃሰት መረጃ በተለያየ መልኩ እየቀረበ መሆኑን የተናገሩት ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ፤ የሁመራ ሱዳን መስመርን የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ቆርጦ መያዙን ቢያስተባብሉም ቦታው ድረስ ሄደው በምስል የተደገፈ መረጃ ማቅረብ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
በአከር እና ዳንሻ በመከላከያ ተይዘው ሳለ የአጥፊው ህወሃት ቡድን በየጊዜው ለማደናገር የተሳሳተ መረጃ ቢያቀብልም እቅዱ አልተሳካለትም ። የከሃዲው ቡድን የመኖር እድሜውን ለማራዘም ከሚጠቀምባቸውን የማደናገሪያ መረጃዎች ህዝቡ አውቆ ሊጠነቀቅ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።