ግጭቱ ከትግራይ ህዝብ ጋር ሳይሆን በህወሓት እና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ነው – የፈንቅል እንቅስቃሴ የትግራይ ወጣቶች አስተባባሪ

“ግጭቱ ከትግራይ ህዝብ ጋር ሳይሆን በህወሓት እና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ነው”- አቶ ሚኪ ተስፋዬ፣የፈንቅል እንቅስቃሴ የጋራ አመራር እና የትግራይ ወጣቶች አስተባባሪ
******************************
Image may contain: 1 person, stripes and closeup

አቶ ሚኪ ተስፋዬ፣የፈንቅል እንቅስቃሴ የጋራ አመራር እና የትግራይ ወጣቶች አስተባባሪ

(ኢፕድ) – በሴራ ፖለቲካ አራማጁ ህወሓት ምክንያት የተቀሰቀሰው ግጭት ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚካሄድ ሳይሆን በህወሓት እና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የሚደረግ መሆኑን የፈንቅል እንቅስቃሴ የጋራ አመራር እና የትግራይ ወጣቶች አስተባባሪ ገለጸ።

የፈንቅል እንቅስቃሴ የጋራ አመራር እና የትግራይ ወጣቶች አስተባባሪ አቶ ሚኪ ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የሴራ ፖለቲካ አራማጁ ህወሓት እድሜውን ለማራዘም የመጨረሻ አማራጭ ያለውን ጥቃት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ሰንዝሯል። ይሄን ተከትሎ በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ፈንቅል የሚቀበል ነው። ግጭቱ ግን ከትግራይ ህዝብ ጋር ሳይሆን በህወሓት እና በመላው ኢትዮጵያን መካከል መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል።
የፈንቅል ንቅናቄ አባላት የህወሓት አቋም በትግራይ ክልል ውስጥ በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ ትግል ህወሓትን ማስወገድ እንደማይቻል፤ ስልጣኑንም ለትግራይ ህዝብ እንደማያስረክብ አምነው፤ ህወሓት ሊወገድ የሚችለው እሱ በታጠቀው ልክና አግባብ እኛም ተደራጅተን በህዝባዊ አመጽ ማስወገድ አለብን የሚል አቋም ይዘው መነሳታቸውን አመልክተዋል ።
ህወሓት ቀደም ሲል ለ27 ዓመት ሲገዛ የነበረበት አቋሙን አለመቀየሩ እና ትግራይ ውስጥ ከገባ በኋላ ይሄንኑ አቋም ይዞ ቀጥሏል። እስካሁንም ከፌዴራል መንግሥቱ ባፈነገጠ መንገድ መከላከያን ከሁለት ለመክፈል ከሚፈጽመው ሴራ ባለፈ፤ የኢትዮጵያ ህዝብም እርስ በእርሱ እንዲጨፋጨፍ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል። አሁን ላይ በመከላከያ ላይ ጥቃት እስከመፈጸምም መድረሱን አስታውቀዋል።
“ከህወሓት የቀደመ ባህሪ አንጻር እኛ ጠብቀነው የነበረው በራሱ በህዝቡ ላይ እንደሚፈጽሙት ነበር፤” ያለው አቶ ሚኪ፤ ይሄን የጠበቁበት ምክንያትም ከዚህ በፊት ሲደረጉ የነበሩ ሴራዎችም ይሄንኑ ስለሚያሳዩ እንደሆነም ገልጿል።
በህወሓቶች በኩል መከላከያውን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ብዙ ሴራዎች ሲሰሩ እንደነበረ፤ ማህበረሰቡም ከሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ ጦርነት እንዲገባ እና ወጣቱም በዛ ስሜት እንዲቀረጽ ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር በመጠቆምም፤ ፈንቅል ይሄን ታሳቢ በማድረግ በማህበራዊ ሚዲያዎች ብዙ ሲያጋልጡ መቆየቱን ተናግሯል።
አቶ ሚኪ እንደሚለው፤ ህወሓት ከትናንት በስቲያም በመከላከያ ላይ ጥቃት የፈጸመበት ትልቁ ምስጢር፣ የፌዴራል መንግሥት ጦር እንደማያዘምትበት በመረዳቱ እና በተደጋጋሚ የህወሓትን የጦርነት አጀንዳ እያከሸፈበት ስለመጣ የመጨረሻ ምሽጉ እየተሰበረ ስለሄደ ነው፤ ያለው አማራጭ ራሱ የፌዴራል መንግሥትን መተንኮስ ስለሆነ ነው። ለዚህ ትንኮሳው ደግሞ ዒላማ ያደረገው መከላከያ እና የአማራ ክልልን ነበር ብሏል።
የመጨረሻ ካርዱን ተጠቅሞ እድሉን ለመሞከር ይሄንን ጥቃት ፈጸመ። በዚህ ረገድ በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል አዋሳኝ ያሉ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች አጠቃላይ በተለይ የአማራ ክልል መንግሥት፤ የትግራይን ህዝብ እና ህወሓትን ነጥሎ ማየት እንደሚጠበቅበት አሳስቧል። የትግራይ ህዝብን ከልዩ ኃይሉና ከህወሓት መለየት ከተቻለ ድሉ የሁሉም ህዝብ ይሆናል። ምክንያቱም አሁን ያለው ግጭት ከትግራይ ህዝብ ጋር አይደለም። ግጭቱ አጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብ እና በህወሓት መካከል እንደሆነ አስታውቋል።
የፌዴራል መንግሥት እስከዛሬ ድረስ ትዕግስት አድርጓል ብለን ነው የምናምነው የሚለው አቶ ሚኪ፤ ትንኮሳውን ተከትሎ እየወሰደ ያለው እርምጃም በተመለከተ አረፍዷል ከሚል በስተቀር ደጋፊዎች ነን ሲል ገልጿል። በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ወጣትም ከህወሓት ጋር እየተሰለፈ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከህወሓት የተነጠለ መሆኑንም አስረድቷል።
በዚህም ሑመራና አካባቢው ህዝቡም ሆነ ወጣቱ ሰላማዊ እንቅስቃሴው ላይ መሆኑን፤ ሽሬ አካባቢ ያለው ሚሊሻም ህወሓትን አታስፈልጉንም የሚል አቋም መያዙን ጠቁመዋል። አሁንም የትግራይ ህዝብና ወጣት ይሄንኑ የተረጋጋና ብስለት የተሞላበት አካሄድ መከተል እንዳለበት አሳስቧል።
አቶ ሚኪ እንደሚለው፤ የትግራይ ህዝብና ወጣት ደግሞ በዚህ መልኩ ከህወሓት ራሱን ሲነጥል አሁን ላይ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ መስራት ያለበት ነገር አለ። ምክንያቱም ህወሓት የዘራው መርዝ እና እሱ ያደራጃቸው ኃይሎች በየክልሉ አሉ።
እነዚህ ኃይሎች በፋይናንስ ሲደግፋቸው የነበሩ ናቸው። እናም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በየቀበሌውና በየወረዳው ተደራጅቶ በንቃት መከታተልና መቆጣጠር አለበት። ይሄን ማድረግ የሚችልበት እድልም ሰፊ በመሆኑ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል ብሏል።
የፌዴራል መንግሥትም ሆነ መከላከያ ደግሞ የትግራይ ሚዲያዎችን በአስቸኳይ በቁጥጥር ሥር አውሎ ለትግራይ ህዝብ ሙሉ መረጃ ማቀበል አለበት ብለን እናምናለን። ምክንያቱም መረጃ አስፈላጊም ለህዝቡ ትልቅ አቅምና መሳሪያም ስለሚሆን፤ በመከላከያው የሚገኙ ድሎች ጭምር በፌዴራል መንግሥት በኩል ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃ መድረስ ይኖርባቸዋል።
በዚህ መልኩ ከተሰራም መልካም ውጤት እንደሚገኝ እናምናለን። ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ህዝብ የተጨቆነ ህዝብ ስለሆነ ከህወሓት የሚጠጋበት ምንም ምክንያት የለም። አሁን ህወሓት ተደግፎ ያለው ሙሉ በሙሉ በልዩ ኃይልና በሚሊሻ ነው። ይህ ደግሞ ከመከላከያ እንደማይዘል አስታውቋል።
የትግራይ ህዝብና ወጣት እንዲሁም የፈንቅል አባላት አሁንም የሰላሙን አቅጣጫ ይዘን ከመከላከያ ጎን መቆም አለብን። መከላከያው ይህ ጥቃት የተፈጸመበት ደግሞ በንጹህ ልብ አገር እየጠበቁ ባሉበት ወቅት እንደመሆኑም፤ ወጣቱ እንደ ወጣት፣ ህዝቡም እንደ ህዝብ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው ከመከላከያ ጎን በመሆን መከላከያን ማገዝ እንደሚገባም አስታውቋል።
የትግራይ ልዩ ኃይልም የህወሓት የሴራ ፖለቲካ መጠቀሚያ ከመሆን ይልቅ ከመከላከያ ጎን ተሰልፎ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን። የትግራይ ህዝብም ከኢትዮጵያዊነቱ ተነጥሎ የሚታይ ህዝብ አይደለም።
ችግሩን አብሮ ታግሎ አብሮ መሻገር ይገባል፤ ህወሓት አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻርም በዚህ መልኩ የሚደረግ ትግል ከሁለት ቀን የሚያልፍ አይሆንም። ለመከላከያችን ሞራል መስጠት አለብን ሲልም አቶ ሚኪ መልዕክት አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን