የጥቅምት ወር የዋጋ ግሽበት በ19.3% ጨምሯል

የጥቅምት ወር የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ19.3% ጨምሯል!

የዘንደሮው ጥቅምት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በ19.3 በመቶ ከፍ ማለቱን ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ገልጿል።

የጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም የምግብ ዋጋ ግሽበትም ካለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ጋር ሲነፃፀር በ23 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቅሷል።

በጥቅምት ወር በአብዛኞቹ የእህል ዓይነቶች ላይ የታየው ጭማሪ ለምግብ ዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ኤጀንሲው አስታውቋል።

በዳቦ፣ እንጀራ፣ ስኳር፣ ከውጭ የሚገባ የምግብ ዘይት፣ ድንች፣ በርበሬ እና የቡና ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱም ለዋጋ ግሽበት መጨመር ምክንያት መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

በአንፃሩ በበቆሎ፣ ስንዴ፣ አትክልትና አንዳንድ የጥራጥሬ እህል ዓይነቶች ላይ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ መመዝገቡም ተገልጿል።

ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች የዋጋ ግሽበት የጥቅምት 2013 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ14 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ኤጀንሲው ገልጿል።

በአልኮል፣ ትምባሆ፣ ጫት፣ የቤት ማፅጃ እና ኢነርጂ (የማገዶ ከሰል)፣ የቤት መስሪያ ቁሶች፣ የህክምና እና ጌጣገጥ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ግሽበት ከፍ እንዲል ማድረጉም ተመልክቷል።

የጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው መስከረም ወር ጋር ሲነፃፀር በ0 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ኤጀንሲው ገልጿል። (ENA)