የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ግንኙነትና ደኅንነት ፖሊሲ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቦሬሌ የተመራ ልዑካን ቡድን ከሁለት ሳምንት በፊት ከፌዴራል መንግሥትና ከትግራይ ክልል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ እንዲሁም በሁለቱም መንግሥታት ገዥ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር መወያየታቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የኅብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በወቅቱ ተገናኝተው መምከራቸውን ሪፖርተር ከምንጮች ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኅብረቱ ከፍተኛ ልዑካን ወደ ትግራይ ክልልም በማምራት፣ ከክልሉ መንግሥት አመራሮች፣ እንዲሁም ከደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር መወያየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይኼው ቡድን በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋርም በአካል ተገናኝቶ የመከረ ሲሆን፣ ይህንንም የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑ አቶ ጌታቸው ረዳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሕወሓትን በመወከል ከኅብረቱ ልዑካን ጋር ውይይት ካደረጉት መካከል አንዱ እሳቸው እንደነበሩ የገለጹት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የኅብረቱ ከፍተኛ ልዑክ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ያለውን አለመግባባት መሠረታዊ ምክንያቶች ለማወቅ ጥያቄ አቅርቦ ማብራሪያ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡
የኅብረቱ ልዑካን ቀጣይ ውይይት እንደሚኖር እንደገለጹላቸውም ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ለሚገኘው ሰሜን ዕዝ ምክትል ዋና አዛዥ የላከ ቢሆንም፣ የትግራይ ክልል መንግሥት የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ ሆነው አዲስ የተመደቡትን ሜጀር ጄኔራል በላይ ሥዩም ወደ መቀሌ እንዳይገቡ ከልክሏል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የጠየቅናቸው አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ የተመደቡት ዋና አዛዥ ከድሬዳዋ ወደ ትግራይ ከመምጣታቸው አስቀድሞ የክልሉ መንግሥት እንደማይቀበላቸው አስታውቆ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ይህ ውሳኔ ከግለሰቡ ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ የሚገልጹት አቶ ጌታቸው፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. አንስቶ ሥልጣን ላይ ያለው የፌዴራል መንግሥት የሚተላለፉ ውሳኔዎችን እንደማይቀበል አቋም ከመያዙ የመነጨ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በሚመራው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የሚወስነው የአመራር ለውጥ በትግራይ ክልል ጋር እንዴት እንደሚገናኝ እንዲያብራሩ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው፣ ዓላማው የአመራር ለውጥ ብቻ ሳይሆን በሰሜን ዕዝ ውስጥ ያለውን ሠራዊት አዲስ ወደሚቋቋመው የምዕራብ ዕዝ ለማዘዋወር ያለመ ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹አገር መዳን ካለበት ይህ ሠራዊት መነካት የለበትም፤›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ይህንን የምንለው ከደኅንነት ሥጋት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን አገር ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የዚህ ጦር ባህርይና መገለጫ ማንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ መደረግ አለበት ከሚል እምነትና ውሳኔ የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡