የሰኔ 16ቱ ፍንዳታ ነገር (ከዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ እውነታዎች)

የሰኔ 16ቱ ፍንዳታ ነገር (ከዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ እውነታዎች)
============ ሚኪያስ ሰብስቤ ================
ምርመራው
======
ሁለት አይነት ምርመራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
አንደኛው ምርመራ በፍንዳታው ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎችን የተመለከተ ነው፡፡
ሌላኛው በስራቸው ክፍተት አሳይተዋል በሚል የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ሃላፊዎች እና አባላት የሚገኙበት ነው፡፡
በጠቅላላው እስካሁን 18 ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን በሁለቱም የምርመራ ሂደቶች ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የመያዣ ትዕዛዝ መውጣቱን መርማሪዎች ተናግረዋል፡፡
ምርመራዎቹም በአራት የተለያዩ መዝገቦች በመከናወን ላይ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ምርመራው ክፍተት በማሳየት በተጠረጠሩ ግለሰቦች እና በፍንዳታው ቀጥታ ተሳትፎ አላቸው በተባሉ ግለሰቦች መካከል ግንኙነት መኖሩን እስካሁን አላመለከተም፡፡

ተጠርጣሪዎች
=======
ክፍተት በማሳየት
ክፍተት አሳይተዋል በሚል የተጠረጠሩት የጸጥታ አካል አባላት መካከል የአ.አ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርን ጨምሮ 10 ተጠርጣሪዎች ይገኛሉ፡፡
ከተጠርጣሪዎች ውስጥ አራቱ የኮማንደር ማዕረግ ያላቸው ሲሆን፤ ሁለቱ የምክትል ኮማንደር፣ አንዱ የምክትል ኢንስፔክተር እና ሁለቱ የዋና ሳጅን ማዕረግ አላቸው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በሙሉ የፍንዳታው እለት ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ አነሱን የተመለከተው ምርመራ በመጠናቀቅ ላይ ነው በሚል የአራት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ብቻ ተፈቅዷል፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህ የመጨረሻ የጊዜ ቀጠሮ እንደሚሆን ለመርማሪዎች ገልጸዋል፡፡

ቀጥታ ተሳትፎ
ቀጥታ ተሳትፎ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩት ግለሰቦች ብዛት 8 ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ ዘግይቶ ለእስር የተዳረጉት የብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ተቀም፤ የመምሪያ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጊ ይገኙበታል፡፡
ሶስት የምርመራ መዝገቦችም ተከፍተዋል፡፡
የመጀመሪያው የምርመራ መዝገብ አምስት ተጠርጣሪዎችን የያዘው ነው፡፡ እነዚህ ተጠርጣሪዎች በእለቱ የተያዙ ሲሆን፤ በአማኑኤል ህክምና በመከታተል ላይ ነች ከተባለች አንዲት ተጠርጣሪ በቀር አራቱ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ በቀጣዩ ቀጠሮ ፖሊስ በህክምና ላይ ስለመሆኗ ማስረጃ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡
ለዚህ ምርመራ የሰባት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቅዷል፡፡
በሌላኛው የምርመራ መዝገብ፤ ሁለት ተጠርጣሪዎች የሚገኙ ሲሆን ግለሰቦቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተቃጣ የግድያ ሙከራ ለማድረግ በስልክ ግንኙነት ትዕዛዝ የሰጡ እና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ናቸው በሚል ተጠርጥረዋል፡፡
አንደኛው ተጠርጣሪ የፊቼ ከተማ ነዋሪ እና ከሦስት ወራት በፊት በይቅርታ ከተፈቱት መካከል እንደነበሩ ታውቋል፡፡
በሶስተኛው የምርመራ መዝገብ፤ የደህንነት መምሪያ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጊ ያሉበት ነው፡፡
ተጠርጣሪው ከሌሎቹ ዘግየት ብለው የተያዙ በመሆኑና ቀሪ የምርመራ ስራዎች በመኖራቸው፤ እሳቸውን የተመለከተው መዝገብ ለተጨማሪ ምርመራ የ12 ቀናት ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል፡፡
መርማሪዎች በነዚህ መዝገቦች፤ ከኤፍቢአይ የቴክኒክ ምርመራ ውጤት ለመጠበቅ፤ የፍንዳታው ጉዳት መጠንን በተመለከተ ከህክምና ተቋማት ሰነድ ለማግኘት፤ የአገር መከላከያ አባላት ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ከመከላከያ ሰነድ ለመቀበል፤ ተጨማሪ ምስክሮች ቃል ለመቀበል እና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ተጨማሪ ቀጠሮ ጠይቀዋል፡፡