በአዳማ ከተማ ሃዊ ሆቴል በመደርመሱ የአራት ሰው ህይወት አለፈ

[addtoany]
በአዳማ ከተማ ዛሬ ህንጻ ተደርምሶ ባደረሰው አደጋ የአራት ሰው ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው በአዳማ ደምበላ ክፍለ ከተማ ኢሬቻ ቀበሌ ውስጥ ነው።
በቀበሌው ልዩ ስሙ ኮሮኔል ደጀኔ ስሜ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ያለው ሃዊ ሆቴል በመደርመሱ አደጋው ሊደርስ እንደቻለ አስረድተዋል።ሆቴሉን በአዲስ ህንፃ ለመተካት አሮጌውን እያፈረሱ ባሉት የቀን ሠራተኞች ላይ በደረሰው አደጋ ከመካከላቸው የአራት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን ኢንስፔክተሯ አስታውቀዋል።
አደጋው ያጋጠመበት ስፍራሁለት ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በአዳማ ሪፌራል ሆስፒታል የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የአደጋው መንስኤ የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑንም አመልክተዋል።የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ጸ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ራውዳ ሁሴን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በግንባታ ስፍራ የደረሰው አደጋ ሕይወታቸው ካለፈው 4 ሰዎች በተጨማሪ ሁለት ሰዎች ላይም ከፍተኛ የአካል ጉዳት አስከትሏል።

ይህ አደጋ የተከሰተው ኢሬቻ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው።በስፍራው አንድ አሮጌ ቤት ፍርሶ አዲስ ሕንጻ እየተገነባ ነበር። አሮጌው ቤት ግን ሙሉ በሙሉ እንዳልፈረሰ ተጠቁሟል።የአሮጌው ቤት ግድግዳ እንደ አጥር ሆኖ ሲያገለግል ነበር። ይህ እንደ አጥር ሆኖ ሲያገለግል የነበረ የአሮጌ ቤት ግድግዳ ተደርምሶ ነው በቀን ሰራተኞች ላይ ጉዳቱን ያስከተለው ሲሉ ወ/ሮ ራውዳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።የጸ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ራውዳ ግንባታው ከመጀመሩ በፊት የአሮጌው ቤት ግድግዳ ሙሉ በሙሉ መፍረስ ነበረበት ብለዋል።

የዓይን እማኞችን ምን ይላሉ?

በግንባታ ስፍራው በቀን ሰራተኝነት የሚሠራው ኢብሳ አያና የተመለከተውን እንዲህ ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ግድግዳውን ለማፍረስ ከስር ቦርብረውት ነበር። ከዛ መልሶ እነሱ ላይ ተደረመሰ። እኛ ሰባተኛ ፎቅ ላይ ነበረን። ጩኸት ሰምተን ስንወርድ እለያቸው ላይ ተደርምሷል”

ኢብሳ እንደሚለው ሠራተኞቹን ከፍርስራሹ ስር ለማውጣት ረጅም ሰዓት ወስዷል።

ግንባታው በሚካሄድበት ስፍራ ነዋሪ እንደሆነች የምትናገረው አስናቁ ደቻሳ ደግሞ ከፍርስራሹ የአራት ሰዎች አስክሬን ሲወጣ መመልከቷን ትናገራለች።

“ሲደረመስ አይቻለሁ” የምትለው አስናቁ በአካባቢው በርካታ ሰዎች በለቅሶ ሐዘናቸውን ሲገልጹ ነበር ብላለች።

በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው አራቱም የቀን ሠራተኞች ወንዶች መሆናቸው ተነግሯል።- ቢቢሲ