ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ የፓርክነት ህልውናውን ሙሉ ለሙሉ ለማጣት መቃረቡ ታውቋል።

ጂ ኤም ኤን – በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የሚገኘው ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ የፓርክነት ህልውናውን ሙሉ ለሙሉ ለማጣት መቃረቡ ታውቋል።
ላለፉት ዓመታት በዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ ያሳለፈው ፓርኩ አሁን ላይ የደረሰበት የአደጋ ደረጃ ህልውናውን ሙሉ በሙሉ የሚያሳጣ ስለመሆኑ ጂ ኤም ኤን ሰምቷል።
ባሳለፍነው ዓመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፓርኩን ከጎበኘ በኋላ ህልውናው አደጋ ውስጥ ነው በሚል ለመንግስት ማሳወቁ ይታወሳል።
ለፓርኩ አሁን የደረሰበት ደረጃ መድረስ ህገወጥ ሰፈራ፣ የከብቶች ግጦሽ፣ አደን፣ የደን ጭፍጨፋ፣ ወደፓርኩ ክልል ሰርጎ የገባው ኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን እንቅስቃሴ፣ በኦሮሚያ ክልል በኩል የቀረበ ድርሻ ይገባኛል ጥያቄ ወዘተ ይገኙበታል።
በ1974ዓ.ም ብሄራዊ ፓርክ ተብሎ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ነጭ ሳር በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን የሚገኝ የሀገር ሀብት በሚል ጥበቃ ሲደረግለት መጥቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በፓርኩ ምስራቃዊ ክፍል በኩል ጋሞ ዞንን የሚያዋስነው ኦሮሚያ ክልል የይገባኛል ጥያቄ አንስቶበታል።
ይህንን ተከትሎም ኦሮሚያ ክልል በርካታ ቁጥር ያላቸውን የክልሉን አርብቶ አደር ማህበረሰቦችን ወደፓርኩ ክልል አስገብቶ በማስፈር ለህልውናው አደጋ ውስጥ መግባት ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አመራር ለጂ ኤም ኤን ገልፀዋል።
የደቡብ ክልል መንግስት የነጭ ሳር ህልውናን ለመታደግ የሚደረገው ጥረት ከአቅሜ በላይ ነው በሚል በጉዳዩ ላይ የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ባሳለፍነው ዓመት ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
እንደኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዮት መረጃ ከሆነ ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ 20 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ብዝሃ ህይወት በውስጡ አቅፎ ይዟል።