አሁን ባለው ሁኔታ ትራምፕ የማሸነፍ እድሉ የመነመነ ነው #ግርማካሳ

የአሜሪካን ፖለቲካና ምርጫን በተመለከተ ብዙ ግንዛቤ ለሌላቸው ወገኖች የሚከተለውን አጭር ትንተና እንደሚከተው አቀርባለሁ፡፡
አሜሪካ 50 ስቴቶች አሉ፡፡ የአገሪቷ ፕሬዘዳንት የሚመረጠው በየ አራት አመቱ ነው፡፡ እጩ ተወዳዳሪዎች ምን ያህል ህዝብ ድምጽ አገኙ (popular vote) የሚለው ሳይሆን ምን ያህል ስቴቶችን አሸናፊ ሆነ፣ ምን ያህል ኤሌክቶራል ኮሌድ የሚሉት አገኘ የሚለው ነው የሚታየው፡፡
ሁሉም ስቴቶች አንድ አይነት አይደሉም፡፡ ስቴቶች እንደ ሕዝብ ብዛታቸው የተወሰነ ድምጽ ይሰጣቸዋል፡፡ Electoral college or electoral vote ይሉታል፡፡ ለምሳሌ ካሊፎርኒያ 56 ኤሌክቶራል ድምጽ አላት፣ ቴክሳስ ደግሞ 38፡፡ ዋሺንገትን ዲሲ 3 ሲኖራት፣ የጆ ባይደን አገር ዴላዌርም 3 አላት፡፡
እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም ከጆርጅ ቡሽ በላይ ብዙ ሕዝብ የመረጠው አል ጎርን ነበር፡፡ ከአራት አመት በፊት ደግሞ ብዙ ሕዝብ የመረጠው ዶናልድ ትራምፕን ሳይሆን ሂልሪ ክሊንተንን ነበር፡፡ ግን ፕሬዘዳንት የሆኑት ቡሽና ትራምፕ ናቸው፡፡
ለምሳሌ በካሊፎርኒያ 10 ሚሊዮን፣ በቴክሳስ 8 ሚሊዮን፣ በፍሎሪዳ ደግሞ 6 ሚሊዮን መራጭች መረጡ እንበል፡፡ አንድ ተወዳዳሪ ከ10 ሚሊዮን የካሊፎርኒያ ነዋሪ 9ኙን ፣ ከቴክሳስ 3ቱን ፣ ከፍሎሪዳ ደግሞ 2ቱን ቢያሸነፍ በአጠቃላይ 14 ሚሊዮን የሕዝብ ድምጽ አገኘ ማለት ነው፡፡ ያኛው ተወዳዳሪ ደግሞ ከካሊፎርኒያ 1 ሚሊዮን፣ ከቴክሳስ 5 ፣ ከፍሎሪዳ ደግሞ 4 ሚሊዮን ቢያሸነፍ 10 ሚሊዮን የሕዝብ ድምጽ ያገኛል፡፡፡ ኤሌክቶራል ድምጽን ካየን ግን 10 ሚሊዮን ድምጽ ያገኘው 67 ድምጽ ሲኖረው፣ 13 ሚሊዮን የሕዝብ ድምጽ ያገኘው ግን 56 ነው የሚኖረው፡፡ አሜሪካኖች እንግዲህ ይህ አይነት አሰራር ነው ያላቸው፡፡ይሄም በተወሰነ መልኩ ዴሞክራቲክ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው።
ሌላ ምሳሌ ላቅርብ።፡ለምሳሌ በፍሎሪዳ መራጩ 5 ሚሊዮን ነበረ ብለን ብንወስድ፣ አንዱ ተወዳዳሪ  2500001 ድምፅ ቢያገኝ፣ ሌላው ደግሞ  2499999 ቢያገኝ ልዩነቱ አንድ ድምጽ ብቻ ነው የሚሆነው። 2500001 ድምጽ ያገኘው 29ኙንም የፍሎሪዳ ኤሌክቶራል ድምጽ ይወስዳል። 2499999 ድምጽ ያለው በአንድ ድምጽ ስለተበለጠ ዜሮ ኤሌክቶራል ድምጽ ነው የሚያገኘው።   249999 እንዳልመረጡ ነው የሚቆጠረው:: በአገር ደርጄ popular vote ቢሆን ኖሮ ግን ይቆጠሩ ነበር።
በየአስር አመቱ የሕዝብ ቆጠራ ይደረጋል፡፡ በሕዝብ ቆጠራው ውጤት መሰረት ለስቴቶች የሚሰጠው የኢሌክቶራል ኮሌጅ ቁጥር ይለያያል፡፡ ከ20 አመታት በፊት ለምሳሌ ኒው ዮርክ 31 ነበራት፡፡ አሁን 29 ሆናለች፡፡
እንግዲህ ከታች የተቀመጠውን ካርታ ብንመለከት፣ ሪል ክርሊር ፖሊቲክስ የተባለው ተቋም ይፋ ባደረገው የሕዝብ አስተያየቶች አማክኝ ድምር፣ በ18 ስቴቶች ትራምፕ ያሸንፋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ከነዚህ ስቴቶች ወደ 125 ኤሌክቶራል ድምጽ ያገኛል ነው የሚባለው፡፡
ባይደን በ20 ስቴቶች ያሸንፋል ወይንም ከ6% በላይ በሕዝብ አስተያየት ይበልጣል ተብሎ ይገመታል፡፡ በአጠቃላይ 268 የኤሌክቶራል ድምጽ ያገኛል ማለት ነው፡፡
ሌሎች 8 ስቴቶች battle grounds/ toss-Ups ስቴቶች ናቸው፡፡ በሰባቱ እነርሱም በዊስኮንሲን ( 10 ድምጽ) ባይደን በ5.5% ፣ በፍሎሪዳ ( 29 ድምጽ ) በ4.1%፣ በአሪዞና ( 11 ድምጽ) በ3.1%,, በአዮዋ (6 ድምጽ) እና በኖርዝ ካሮላይና (15 ድምጽ) 1.4% ፣  በኦሃዮ 0.6% (19 ድምጽ) እና በጆርጂያ ( 16 ድምጽ) 0.3% ባይደን በሕዝብ አስተያየት እየመራ ይገኛል፡፡ በአንዱ ስቴት፣ በቴክሳስ ( 38 ድምጽ) ባይደን በ3.2% ይመራል፡፡
ባይደን ከነዚህ ስምንቱ battle grounds ስቴቶች አንዱን ብቻ ካሸነፈ የሚፈለገው 270 ቁጥር ስለሚሞላለት የሚቀጥለው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ይሆናል፡፡ በ5.5% የሚመራበትን ዊስኮንሲንን ብቻ ለምሳሌ ካሸነፈ 278 ይደርስለታል፡፡ የኤሌክቶራል ድምጹ፡፡
ለዚህ ነው ብዙ ፉክክር እንደ ካሊፎርኒያ፣ አላባማ ባሉት ስቴቶች የማናየው፡፡ ካሊፎርኒያን ባይደን፣ አላባማን ትራምፕ እንደሚያይሸነፍ ስለሚታወቅ ዴሞክራቶች አላባማ፣ ሬፑብሊካኖች ደግሞ ካሊፎርኒያ ገንዘብና ጊዜ አያጠፉም፡፡ እነ ዊስኮንሲን፣ ፍሎሪዳ ላይ ግን ብዙ የምርጫ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ከምንም በላይ እጅግ በጣም ውድ የሆነው በbattle grounds ስቴቶች የሚሰጡ ድምጾች ናቸው፡፡ በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዉያን ሄደው ድምጽ መሰጠታቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ አንድ ድምጽ ልዩነት ያመጣል፡፡ ለምሳሌ ከ20 አመት በፊት ቡሽ አልጎርን በፍሎሪዳ ያሸነፈው በ504 ድምጽ ብቻ ነበር፡፡ቡሽ ፍሎሪዳን አሸንፎ 270 ሆኖለት ነው ፕሬዘዳንት የሆነው፡፡ ያኔ አል ጎር 269 ነበር ያገኘው፡፡
ሳጠቃልል አሁን ባለው ሁኔታ ትራምፕ የማሸነፍ እድሉ የመነመነ ነው፡፡ ሆኖም ግን ገና አራት ሳምንት አለ፡፡ ለፖለቲካ አንድ ቀን እጅግ በጣም ረጅም ነው፡፡ ነገሮች ምስቅልቅላቸው ሊወጣ ይችላል፡፡ አንድ በአሜሪካ የታወቀ የስፖርት አሰልጣኝ ነበር፡፡ ዮጊ ቤራ ይባላል፡፡ አንድ አባባል ነበረችው፡፡ ” እስከሚያልቅ ድረስ አላለቀም” (It ain’t over until it’s over) ይል ነበር፡፡ አሁንም ምርጫው እስኪጠናቀቅ ትራምፕ አያሸንፍም ማለት አይቻልም፡፡ አስተያየቶች በጣም ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ነው ይሄን የጻፍኩት፡፡ ደግሞ ትራምፕ ያሸነፈ እንደሆን ይሄን ብለህ አልነበረም ወይ እንዳትሉኝ፡