መንገዳችን ጠማማ እና በጥቅም ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን እንጠንቀቅ! – ብጽዕ አቡነ አብርሃም

‹‹መንገዳችን ጠማማ እና በጥቅም ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን እንጠንቀቅ!›› ብጽዕ አቡነ አብርሃም
(አብመድ) የመስቀል በዓል ስለእምነት፣ ስለፍቅር እና ስለእውነት የተከፈለ መሥዋዕትነት የገለጠው ብርሃን ነው፡፡ የመስቀል በዓል ተምሳሌት ወደቆ መነሳት፣ ተረስቶ መታወስ፣ ሞቶ መዳን፣ ጠፍቶ መገኘት፣ ስለፍቅር መውረድ እና ስለሰው ልጅ ተላልፎ መሰጠትን ሁሉ የያዘ እንደሆነ የሃይማኖቱ አባቶች ያስተምራሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን የመስቀል በዓልን ታሪካዊ ዳራ ሲያስቡ ከቀራኒዮ እስከ ጎልጎታ፣ ከሮም እስከ እስራኤል፣ ከፋርስ እስከ ቁስጥንጥንያ፣ ከአሌክሳንድሪያ እስከ ኢትዮጵያ በፍቅር፣ በእምነት እና በተስፋ የወጡ የወረዱትን ሁሉ እያሰቡ ነው፡፡ የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከሃይማኖታዊ ዳራ አለፍ ብሎ ባህላዊ ገፅታው የሚጎላበትም አካባቢ ቀላል አይደልም፡፡
መስቀል በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲህ ልዩ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ከቤተሰባዊ መሰባሰብ አልፎ የጎረቤት እና የማኅበረሰብ የስብስብ በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል በየግል ቤት ውስጥ ሲከበር አይታይም፡፡ እንደ ግሽን በታላላቅ አድባራት፣ እንደ ከተሞች በአደባባይ እና እንደ ሰፈር በጎረቤት ተሰባስበው የሚያከብሩት በዓል ነው መስቀል፡፡
የመስቀል በዓል ከሰው ልጅ ጥንተ ታሪክ ጋር ቁርኝት አለው ያሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም የበዓሉን ታሪክ የአዳምን በደል በደሙ ለመሻር ከሰማየ ሰማያት ከወረደው የኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ መገለጥ እስከ ቀራኒዮ ተላልፎ መሰጠቱ ድረስ ያንሰላስሉታል፡፡
መስቀል በቀደምት ሮማውያን ዘንድ የሚታወቀው የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ሲያገለግል ነበር፡፡ የክርስቶስ መስቀል ከቀራኒዮ ተራራ ወርዶ የተቀመጠው ሐዋሪያው ቅዱስ ያዕቆብ መንበረ ጵጵስናውን ባደረገባት ጎልጎታ ነበር፡፡ መስቀሉ ሙታንን ሲያስነሳ፤ ሕሙማንን ሲፈውስ፣ ለምፅ ሲያነፃ እና መሰል ተአምራትን ሲያደርግ ያዩት አይሑዳውያን ቅናት አደረባቸውና ከእየሩሳሌም ወጣ አድርገው በቆሻሻ ቦታ ሦስቱንም መስቀሎች ቀበሯቸው፡፡ ይህም ከ300 ዓመታት በላይ ቆሻሻ ሲደፋበት ስለነበር ታላቅ ተራራ ሆነ፡፡
‘‘ባለፉት ዘመናት ዲዮቅሊጢያኖስን በመከራ ያሳለፈችው ክርስትና የድል ብስራት ዜማ የምትሰማበት ቀን ተቃረበ’’ ይላሉ አቡነ አብርሃም ለተከታዮቻቸው፡፡ ወቅቱ 326 ዓ.ም ገደማ በጣሊያኗ ሮም ንጉሥ የነበረው የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ቅድስት እሌኒ ስለመስቀሉ ፍቅር ስትል ከሮም ወደ እየሩሳሌም አመራች፡፡ በእየሩሳሌም እየተንቀሳቀሰች ቅዱሳን ቦታዎችን እና መካነ መቃብሮችን ሁሉ በማየት አብዝታ ብትደሰትም የመስቀሉ ነገር ግን ከውስጧ አልወጣም ነበርና ሳትሰለች ፍለጋዋን ቀጠለች፡፡ ከብዙ ወጣ ውረድና ድካም በኋላ ግን በአዛውንቱ እና ታሪክ አዋቂው ካህኑ ኪራቆስ አማካኝነት የተቀበረበትን ተራራ ለመለየት በቃች፡፡
በመጨረሻም ቅድስት እሌኒ ደመራ ደምራ በእሳት ባቃጠለችው ጊዜ ጭሱ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ስፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አወጣች፡፡ ‹‹ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር መስቀለ ሞቱን ተቀብሎ ይከተለኝ እንዳለ›› ማቴዎስ በወንጌሉ አሉ አቡነ አብርሃም ‘‘መስቀል ለምናምነው ድኅነት ነው፤ ለማያምኑት ግን ሞኝነት ናውና ዛሬ ላይ ያለነው ክርስቲያኖች ስለምናምነውም እየተሳደድንም ቢሆን መስቀሉን ተሸክመን እንከተላለን፡፡ ክርስቲያን ተስፋው እግዚያብሔር ስለሆነ ተስፋ አይቆርጥምና ዘመነ ዲዮቅሊጢያኖስን አሳልፈን ከዘመነ ቆስጠንጢኖስ ነገ እንደርሳለን’’ ብለዋል በመልእክታቸው፡፡
ዘመናት ሲያልፉ የግማደ መስቀሉ የቀኝ ክፍል በግብፅ ይኖር ነበርና በዘመኑ በኢትዮጵያ ነግሠው የነበሩት ንጉሥ ዳዊት መልካም ግንኙነታቸውን ወሮታ ፍቅራቸውን ችሮታ በማድረግ ግማደ መስቀሉን ይሰጧቸው ዘንድ ግብፃውያኑን ጠየቋቸው፡፡ መልካም ምላሽ አግኝተው መስቀሉን ይዘው በመመለስ ላይ የነበሩት ንጉሥ ዳዊት በመንገድ ላይ እያሉ አረፉና ልጃቸው ንግሥናውን ብቻ ሳይሆን መስቀሉንም ተቀብሎ ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ‹‹መስቀሉን በመስቀለኛ ቦታ›› ከፍ አድርጎ በግሸን ደብረ ከርቤ አስቀመጠው፡፡ ብፁዕነታቸው ‘‘ዛሬም የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ወሮታ ከፋዮች እናንተ ናችሁ’’ ያሏቸውን ወጣቶች በፍቅር፣ በተስፋ እና በፅናት ሃይማኖታቸውን እና ሀገራቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡
‘‘ዛሬ የመስቀልን በዓል የምናከብር እኛ እንደ ቅድስት እሌኒ ስለሃይማኖታችን ስንል በፅናት መቆም ያስፈልገናል’’ ያሉት ብፅዕ አቡነ አብርሃም ሰላም፣ ትዕግስት፣ ፅናት እና መከራ የሚፈራረቁ መሆናቸውን አምኖ ዛሬ ክርስቲያኖች፣ ምእመናን እና ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ በመሆናቸው በፅናት መቆም ግድ እንደሚል አሳስበዋል፡፡ ‘‘ክርስትና በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመከራ ጊዜ ምስጋና፣ በሐዘን ጊዜ መፅናናት፣ እየሞቱ እልልታ፣ እየተገፉ ውዳሴ፣ እየወደቁ ሐሴት እና ስንነሳም ይቅርታን እንጂ በቀልን አናስቀድምም’’ ነው ያሉት፡፡
መስቀሉ ሙታንን ስላስነሳ፣ ሕሙማንን ስለፈወሰ እና ተአምራትን ስላደረገ ከተቀመጠበት የክብር ቦታ ወርዶ ቆሻሻ ላይ ተጣለ፡፡ ለ300 ዓመታትም የቆሻሻ ብርድ ልብስ ተደራርቦበት ተራራ ሆነ፤ ሐሰት በእውነት ላይ ለዘልዓልም የምትነግሥ መስሏቸው ነበር፡፡ ዳሩ እውነት ይገለጣል፤ ብርሃንም ይወጣልና ዘመኑ ሲደርስ ከነተአምራቱ ወጣ፡፡ ይህ የዛሬዎቹን ወጣቶች የሚያስተምረው ሐሰት በበዛበት ዓለም ትዕግስት፣ ተስፋ እና ፍቅር ካለ ሁሉም ነገር እንደሚገለጥ ነው፡፡ ጥላቻ፣ መለያየት፣ ግጭት እና ማፈናቀል የዚህ ዘመን እኩይ በመሆናቸው ወጣቶች ይህንን የጥላቻ ክምር ንደው የፍቅር፣ የፅናት፣ የምሥጋና እና የውዳሴ ድልድይ እንዲገነቡም አሳስበዋል፡፡
‹‹መንገዳችን ጠማማ እና በጥቅም ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን እንጠንቀቅ›› ያሉት ብጽዕ አቡነ አብርሃም እግዚያብሔርን ለመከተል ዓለማዊ ምኞትን ስጋዊ ፍላጎትን መናቅ፣ እግዚያብሔርን ለመከተል ስጋዊ ስልጣንና አስተሳሰብን መፀየፍ እንዲሁም ወሳኝነት እና ፅናት መላበስ እንደሚያስፈልግ ለምዕመኖቻቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
‘‘ትህትና፣ አገልጋይነት፣ ወደ ራስ ማንነት መመለስ እና ሃይማኖትን መጠበቅ በዚህ ትውልድ የሚታዩ በጎ ጀምሮች ናቸው’’ ያሉት አቡነ አብርሃም ይህ የወጣቶቹ በጎ ጅማሮ በአባቶች ተግሳፅ፣ በመንግሥት ትጋት እና በታላላቆች አስተምህሮ በፍቅር እና በመቻቻል እንዲጎለምስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መንግሥት ሕዝብን እና ሀገርን ከጥቃት እና ከጉዳት እንዲጠብቅም ጠይቀዋል፡፡