የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማክበር እና ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ስለ ልማት እና ብልፅግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም! – ኢዜማ

የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማክበር እና ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ስለ ልማት እና ብልፅግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም!

ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አባላት እና አመራር በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በግፍ በተገደሉ ዜጎች የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እየገለፀን ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን።

ኢዜማ በክልሉ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደረሰው ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ እና በመንግሥት በኩል የሚሰጡ ችግር ፈቺ ያልሆኑ ምላሾች የችግሩ ምንጭ አካባቢውን ከሚያስተዳድረው የመንግሥት መዋቅር እና ችግሩን በቸልታ እያየ ያለው የፌደራል መንግሥት ነው ብለን እንድናምን አስገድዶናል። ከዚህ በፊት የተፈፀሙ ጥቃቶች አጥፊዎች እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮች ላይ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ባለመወሰዱ ችግሩ አሁንም ቀጥሏል። ኢዜማ ክልሉን በሚመሩት ኃላፊዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ እርምጃ ካልተወሰደ ግድያና ማፈናቀሉ ይቆማል ብሎ አያምንም። የፌደራል መንግሥት እንደዚህ ዓይነቱ ጥቃቶች ከመድረሳቸው በፊት የመከላከል እና በቶሎ የማስቆም ሥራ ከምንም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለን እናምናለን።

የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን በሕይወት መኖር ማክበር እና ማስከበር ነው። ይሄን ማድረግ ያልቻለ መንግሥት ስለ ልማት እና ብልፅግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም።

የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት
መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም