ዐቃቤ ሕግ በአርበኞች ግንቦት 7 የተከሰሱት ክስ ሊቋረጥ አይገባም ሲል ተከራከረ።

ዐቃቤ ሕግ በአርበኞች ግንቦት 7 የተከሰሱት ክስ ሊቋረጥ አይገባም ሲል ተከራክሯል

(ጌታቸው ሺፈራው)

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የአርበኞች ግንቦት 7 ስም ከፀረ ሽብር አዋጁ ቢነሳም በስሙ የተከሰሰሱት ክሳቸው መነሳት የለበትም ሲል መከራከሩ ታውቋል። ዛሬ ሐምሌ 10/2010 ዓም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በአርበኞች ግንቦት 7 ከተከሰሱት እነ ሚፍታህ ሸሕ ሱሩር ክስ መዝገብ ከተከሰሱት 77 ግለሰቦች መካከል ያልተፈቱት 46 ተከሳሾች የቀረቡ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ክሳቸው መቋረጥ የለበትም ሲል ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱ የተወካዮች ምክር ቤት አርበኞች ግንቦት 7 ከፀረ ሽብር አዋጁ ስሙ እንዲነሳ ካደረገ በኋላ የሽብር ክሶች እንዲቋረጡ “የስራ መመርያ” ይተላለፋል ብሎ እየጠበቀ እንደነበር፣ ነገር ግን እንዳልደረሰው ገልፆአል።

ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ድርጅት ስም ከፀረ ሽብር አዋጁ መነሳቱን በመግለፅ መፈታት እንዳለባቸው ቢገልፁም ዐቃቤ ሕግ “ድርጊቱ የተፈፀመው የድርጅቱ ስም ከፀረ ሽብር አዋጁ ከመነሳቱ በፊት ነው። የድርጅቱ ስም ከአዋጁ በመነሳቱ ብቻ ክሳቸው ሊቋረጥ አይገባም። ክርክሩ መቀጠል አለበት።” ሲል ከፀረ ሽብር አዋጁ ስማቸው በተነሳለቀቸው ድርጅቶች ስም የተመሰረተው የሽብር ክስ መቋረጥ የለበትም ሲል ተከራክሯል።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፀረ ሽብር አዋጁ ክስ የተመሰረተባቸው ክሳቸው ተቋርጦ እንዲሁም በምህረት እንደሚፈቱ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል።

ከሶስት ቀን በፊት ከዐቃቤ ሕግ መስርያ ቤት የተወከለ ሰው ቂሊንጦ እስር ቤት እስረኞችን ባወያየበት ወቅት በሽብር ተከስሰው ያልተፈቱት አቤቱታ ሲያቀርቡ “በዚህ ክስ ተከስሶ እስካሁን እስር ቤት ያለ ሰው ስለመኖሩ አናውቅም” የሚል መልስ እንደሰጣቸው ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል።

ፍርድ ቤት ተገኝቶ የሚከራከረው የዐቃቤ ሕግ መሰርያ ቤት ሰራተኛ በበኩሉ “ክሱ መቋረጥ የለበትም” ሲል ተከራክሯል። የድርጅቱ ስም ከፀረ ሽብር አዋጁ በተነሳበትና አመራሮቹም ወደ ሀገር ይገባሉ በተባለበት ወቅት ተከሳሾቹ በእስር መሰቃየት እንደሌለባቸውም አመልክተዋል።

ፍርድ ቤቱም “የድርጅቱ ስም ከፀረ ሽብር አዋጁ መነሳቱን ብንሰማም፣ የስራ መመርያ አልደረሰኝም” በሚል ለሀምሌ 17/2010 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።