በትግራይ ክልላዊ ምርጫ ህወሓት በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ ሊያሸንፍ እንደሚችል ተነገረ

በትግራይ ክልላዊ ምርጫ የተሳተፉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገዢው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ ሊያሸንፍ እንደሚችል ተናገሩ።
ትናንት ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሔደው ክልላዊ ምርጫ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈውበታል።
የትግራይ ነጻነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ግርማይ በርኸ “ህወሓት ምክር ቤቱን መቶ ፐርሰንት ይቆጣጠራል ብዬ እፈራለሁ። ለማንኛውም ውጤቱን ማየት ነው” ሲሉ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። የሳልሳይ ወያነ ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ጎደፋይ በበኩላቸው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ከክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች 98 ወይም 99 በመቶውን ሊያሸንፍ እንደሚችል ቅድመ ግምታቸውን ተናግረዋል።
የምርጫው የመጀመሪያ ውጤት ዛሬ ማምሻውን ይፋ ሊደረግ ይችላል። የትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው መርሐ ግብር መሠረት አጠቃላይ የምርጫው ውጤት መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም ይገለፃል።
የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርያም የምርጫ ውጤቱን አዝማሚያ ለመናገር ጊዜው ገና ቢሆንም ህወሓት በከፍተኛ ልዩነት ቢያሸንፍ እንደማይገረሙ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ህወሓት “በጣም ጠንካራ ነው” ያሉት ሙሉወርቅ “ይኸ ከዚህ በፊትም የተረጋገጠ ነው” ሲሉ አክለዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት «የማይፀና እና ተፈፃሚነት የሌለው» ይሆናል ባለው ምርጫ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል። እነሱም ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት)፣ ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና)፣ የአሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ዓዴፓ) እንዲሁም የትግራይ ነፃነት ፓርቲ (ውናት) ናቸው።