የትግራይ ክልል ምርጫውን ለመታዘብ የጠየቀ አንድ ተቋምን ማገዱ ተገለጠ

የትግራይ ክልል ምርጫውን ለመታዘብ የጠየቀ አንድ ተቋምን ማገዱ ተገለጠ
DW : «ሰብ ሕድሪ ሲቪል ማሕበረሰብ ትግራይ» የተባለ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ ነፃ ተቋም በትግራይ ምርጫ ለመታዘብ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ እንደተደረገበት ገለፀ፡፡
ሰብ ሕድሪ ሲቪል ማሕበረሰብ ትግራይ ያወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው ተቋሙ «ታሪካዊ» ባለው የትግራይ ምርጫ በታዛቢነት ለመሳተፍ 300 ገደማ አባላቱን ለታዛቢነት አዘጋጅቶ ነበር። ቢሆንም የትግራይ ምርጫ ኮምሽን ከሦስተኛ ወገን በቀረበለት ቅሬታ ከታዛቢነት እንዳገደው ዐስታውቋል፡፡
ሰብ ሕድሪ ሲቪል ማሕበረሰብ ትግራይ በትግራይ ምርጫ ኮምሽን የተላለፈውን የእግድ ውሳኔ «ተገቢነት የሌለው» ብሎታል፡፡
የትግራይ ምርጫ ኮምሽን በበኩሉ ሲቪል ተቋሙ በምርጫው ከሚወዳደር ፓርቲ ቅሬታ ስለቀረበበት ነገ ይካኼዳል በተባለው ምርጫ ተሳታፊ እንዳይኾን መወሰኑን ገልጧል፡፡
ሰብ ሕድሪ ሲቪል ማሕበረሰብ ትግራይ ሰኔ 2010 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ በትግራይ «ዴሞክራታይዜሽን» እና ክብሮች ዙርያ የሚሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ይኽ በእንዲህ እንዳለ፦ የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን ለ61 የሀገር ውስጥ ተቋማት ምርጫውን እንዲታዘቡ ፍቃድ መስጠቱን ዐስታውቋል፡፡
በትናንትናው እለት አራት ጋዜጠኞችን ጨምሮ የትግራይ ክልል ምርጫን ለመከታተል ወደ መቀሌ በአየር ሊጓዙ የነበሩ ዐሥራ ኹለት ሰዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንደታገዱ ተነግሯል። ከታገዱት መካከል የሀገር ውስጥ እና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች እንደሚገኙበትም ተዘግቧል።