ምክትል ኢታማጆር ሹሙ ጄኔራል ብርሐኑ ጁላ ለአዲስ ዘመን የሰጡት ቃለ ምልልስ

ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ ካሏት ባለ አራት ኮኮብ ሙሉ ጄኔራሎች አንዱ ናቸው፡፡ ትውልዳቸው በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ወረዳ ኩየራ አካባቢ ሻሻ ቀበሌ ጥር 27 ቀን 1957 ዓ.ም፡፡ የደርግን ሥርዓት ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል ተሳትፈዋል፡፡ ከትጥቅ ትግሉ በኋላ የብርጌድ፣ የሬጅመንት፣ የኮር እንዲሁም የማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ፤ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ፤ የተባበሩት መንግሥታት የአብዬ ግዛት ግዳጅ የኃይል አዛዥ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በሰላም ማስከበር ዋና መምሪያ ኃላፊነትም ያገለገሉ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የኦፕሬሽን ኃላፊ በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ጄኔራል ብርሃኑ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ የማስተርስ ዲግሪ ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ የተቀበሉ ሲሆን፤ በሰላምና ደህንነትም ማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአገራዊና ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከጄኔራል ብርሃኑ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ ይላል፡፡

አዲስ ዘመን ፡- በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ መለኪያው ብዙ ነው፡፡ አንደኛው የዘመናዊ ሠራዊት መለኪያ ሠራዊቱ ዓላማውን እንዲያውቅ፣ ለምን እንደተደራጀና እንደሠለጠነ እንዲገነዘብ ተደርጎ ሲገነባ ነው፡፡ ሁለተኛው የዘመናዊነት መገለጫ በወታደራዊ ሳይንስ ጥበብና ዶክትሪን በቂ እውቀት ያለው ሆኖ መገኘት ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በወታደራዊ ባሕል ዙሪያ በቂ እውቀት መጨበጡ ይታያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሰራሮችን፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን ማወቅ ግዴታ ነው፡፡ ደንቦችንና መመሪያዎችን ተከትሎ በሥነ ሥርዓት የሚሠራ፤ ተልዕኮውን ጠንቅቆ የሚያውቅ በከፍተኛ ወታደራዊ ዲስፕሊን የታረቀ ሠራዊት መሆን አለበት፡፡ በሚገባ የተደራጁ ብቁ የሥልጠና ተቋማት ያሉት፤ ሠራዊቱም በዚህ ሂደት ያለፈ መሆን አለበት ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታውን ቀድሞ ከነበረው ሠራዊት ጋር ሲያነፃፅሩት እንዴት ያዩታል ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- ማነፃፀር አይቻልም፡፡ ያን ጊዜ ሠራዊቱ የተደራጀበት ዓላማ፣ ተልዕኮና ወቅቱም ለየት ይላል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ሥርዓት አብዛኛው የሠራዊቱ አካል በብሔራዊ ውትድርና እና በሚሊሺያ መልክ ነው የተመለመለው፡፡ መደበኛ ሠራዊቱ ጥቂት ነው፡፡ መኮንኖቹ በሙሉ የመደበኛ ሠራዊት አባል ናቸው፡፡ በአገሪቱ የምሥራቅ አካባቢ ያጋጠመው ጦርነት እንዲሁም የእርስ በእርስ ጦርነት በስፋት ስለነበር የሰው ኃይል በብዛት አስፈላጊም ስለነበር መደበኛ ያልሆነው ኃይል ይበዛል፡፡ ኦፊሰሮቹን ከወሰድን በደርግ ጊዜም ከደርግ በፊትም በሀገር ውስጥም በውጭም የተማሩ በብዛት ነበሩ፡፡

አዲስ ዘመን፡- አዲስ በተዋቀረው የመከላከያ ሠራዊት ቀድሞ የነበሩት ፕሮፌሽናል የሆኑ መኮንኖች ተካተው ነበር፡፡ አሁንስ እውቀታቸውን ለመጠቀም የመመለሱ ሀሳብ የለም ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- አስፈላጊ በሆነ ቦታም አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ወደፈትም አስፈላጊ በሚሆኑበት ቦታ እንጠቀማለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሌሎች ሀገራት ነፃ ሁነው በተለያየ የሙያ ዘርፍ የሚሠሩ አማካሪዎች በውትድርናው፣ በዲፕሎማሲውና በሌሎችም መስኮች ለመንግሥት ብዙ ይጠቅማሉ፡፡ በዚህ ረገድ የቀደሙትን ባለሙያዎች የመጠቀም ሀሳቡ አለ ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- አሁን ያለው መከላከያ 1985 እስከ 1989 ዓ.ም አካባቢ የነበረው አይነት አይደለም፡፡ አሁን ካዴት የሚያስተምርበት ተቋም አለው፡፡ ስታፍ ኮሌጅ የሚባል አለው፤ ድሮ የነበሩ ቢሆኑም እኛ ስንገባ ፈርሰው ነበር፡፡ በዓይነቱ አዲስ የሆነ የጦር ኮሌጅ (ዋር ኮሌጅ) እየመሰረትን ነው፡፡ ዋር ኮሌጅ ማለት ጦርነትን፣ ፖለቲካን ኢኮኖሚን አጣምሮ በስትራቴጂክ ደረጃ ጥናት የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡

ይህ ለሚሊተሪው ብቻ አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ አመራሩንም ያቅፋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እዚህ ደረጃ ደርሰናል፡፡ በሚገባ የተደራጀ ስታፍ ኮሌጅ፤ በሚገባ የተደራጀ የካዴት ኮሌጅ አለን፡፡ በሚገባ የተደራጀ የጦር ኮሌጅ እያቋቋምን ነው፡፡ ሁለተኛ ተቋሙ የራሱ ሪሰርች ኤንድ ዴቨሎፕመንት ሴንተር አለው፡፡ዶክትሪን የሚያጠና ስትራቴጂ የሚያጠና፤ ቴክኖሎጂ የሚያጠና፤ የዘመኑን ጦርነት የሚያጠና አካል አለ፡፡ የራሳችንን ሙያው፣ እውቀቱና ልምዱ ያላቸውን ሰዎች እንጠቀማለን፡፡ አስፈላጊ ሁኖ ሲገኝ ከውጭም እናመጣለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሠራዊቱ የሰላም ማስከበር ግዳጁን በምን መልኩ እየተወጣ ነው ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ አገራት የሰላም ማስከበር ግዳጁን በጣም በሚያኮራ ደረጃ ነው እየፈጸመ የሚገኘው፡፡ ዝግጁነቱ፣ ብቃቱና ተልእኮውን የመወጣት አቅሙ በተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የተመሰከረለት ነው፡፡ በየትኛውም የግዳጅ ቀጣና ተመራጭ የሆነው የሰላም አስከባሪ ኃይል የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፡- በሠራዊቱ ተጠቃሚነት ረገድ ያለው ሁኔታ እስከምን ድረስ ነው ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- በግዳጅ ስምሪቱ ውስጥ የሠራዊቱን ተጠቃሚነት በተመለከተ በተቋሙ አሰራር መሰረት የሚፈጸም ነው፡፡ ሠራዊታችን በደመወዝና በጡረታ ብቻ የሚሰናበት ሠራዊት አይደለም፡፡ ግዳጅ ላይ ተሰማርቶ እየተሳተፈ ከዚያ ግዳጅ የሚገኘውን ገቢ በተወሰነው ልክ እያገኘ እራሱን የሚደጉምበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለምሳሌም ያህል ኦብዘርቨሮች፣ ስታፍ ኦፊሰሮችና አመራሮች አሉን፡፡እነዚህ የተባበሩት መንግሥታት የሚከፍላቸው ደመወዝ ከእኛ ሀገር ለየት ያለ ስለሆነ ጥሩ የሚባል ነው ብለን እናስባለን፡፡ አገልግሎት የሚሰጡት ለአንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ኃይል ስላለን በተቻለ መጠን ሁሉም እንዲዳረሳቸው ለማድረግ ነው፡፡ በሌሎች ሀገሮች ሲታይ አንድ ሰው ሦስትና አራት ጊዜ የሚላክበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እኛ ጋ ግን ሁሉም ዕድሉን እንዲያገኝ ነው ስንሠራ የቆየነው፤ እየሠራንም ያለነው፡፡

አዲስ ዘመን ፡- በሀገራችን ፖለቲካዊ ቀውስ አጋጥሞ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ በአንዳንድ አገሮች እንደሚታየው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አልተካሄደም፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- ቀደም ሲል እንደገለጽኩት መከላከያ ኃይሉ ፕሮፌሽናል ነው፡፡ ይህ ከሆነ ከሠራዊቱ መገለጫዎች አንዱ የተሰለፈበትን ዓላማ ጠንቅቆ ማወቅ ነው፡፡ ይሄ ሠራዊት የተደራጀው ሕገ መንግሥቱን እንጂ፤ ፓርቲ ለመጠበቅ አይደለም፡፡ በግልጽ በሕገ መንግሥቱ በሰፈረው መሰረት ሠራዊቱ የማንም ፓርቲ ወገንተኛ እንዲሆን አይፈቀድም፡፡ ለማንኛውም ፓርቲ ወግኖ ሀሳብ አይሰጥም፡፡ ይሄ ሠራዊቱ የተደራጀበት መሰረታዊ ዓላማ ነው፡፡ ይሄን ስናይ ሠራዊታችን ሕገመንግሥቱን ነው የሚጠብቀው፡፡

ሕገ መንግሥቱን ማንም ማፍረስ አይችልም፡፡ ሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ሌላ ተቃዋሚ ኃይል ሕገ መንግሥቱን ማፍረስ አይችልም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ግን ተመርጦ ጉድለት አለው፣ መታረም፣ መለወጥና መጨመር አለበት የሚለውን ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊወስን ይችላል፡፡

ሠራዊታችን የሕገ መንግሥት ጠባቂ ነው ሲባል ግልጽ ነው፡፡ ሕገ መንግስቱን ጠባቂ የሆነ ሠራዊት መፈንቅለ መንግስት አያደርግም፡፡ ሀሳቡም ራሱ ነውር ነው፡፡ ምክንያቱም ሕገመንግሥቱ ያስቀመጣቸው መርሆዎች አሉ፡፡ እነዛ መርሆዎች ሥራ ላይ መዋል አለባቸው፡፡ ሠራዊቱ ሀገሩንና ሕዝቡን ጠባቂ ነው እንጂ ፖለቲካዊ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም፡፡ እንደዚህ አይነት መርህ የለውም፡፡

ሌላው ነጥብ የእኛ ሠራዊት መፈንቅለ መንግሥት ቢያደርግ አደገኛ ነው፡፡ መፈንቅለ መንግሥት ማድረግ በሠራዊቱ የግንባታ አቅጣጫዎች ላይ ክልክል ነው፡፡ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይሄንን ጥሶ መፈንቅለ መንግሥት አደርጋለሁ ብሎ የሚሞክር ኃይል ካለና ቢሞክር ራሱ ነው የሚጠፋው፡፡ ሠራዊቱ በዚህ የተገነባ ነው፡፡ ስለዚህ የማይታሰብ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፡- በተለያዩ ክልሎች ግጭት ሲፈጠር ሠራዊቱ በመንግሥት ሲጠየቅ ጣልቃ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የነበረው የሠራዊቱ ሚና እንዴት ይታያል ? አንዳንድ ጊዜ ኃይል አብዝቶ ይጠቀማል የሚሉ አስተያየቶች በስፋት ይሰማሉ፤ ይሄንን እንዴት ነው የሚያዩት ?

ጄኔራል ብርሃኑ ፡- እውነት ነው፡፡ እንደዛ እየሠራን ነው ሀገሪቱን ያቆየነው፡፡ ችግር በተፈጠረበት ሁሉ እየገባን እያገዝን ፖለቲከኛው የፖለቲካ ሥራውን ሰርቶ ከዛ ውስጥ እንድንወጣ ፋታ እንዲያገኝ ስናደርግ የነበረው፡፡ በዚህ አፈጻጸም ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች አሉ፡፡ የበዛ ኃይል(ኤክሰስ ፎርስ )ተጠቅሟል የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ ኤክሰስ ፎርስ (የበዛ ኃይል) የሚለውን መተርጎም ማብራራት ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኤክሰስ ፎርስ (የበዛ ኃይል) የሚለው እንዴት ነው የሚገለጸው ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- የራሱ መለኪያዎች አሉት፡፡ የሆነ ሰው ተነስቶ ኤክሰስ ፎርስ ተጠቅመዋል በሚል በማህበራዊ ድረ ገጽ ይጽፋል፡፡ አንዳንድ የዳበረ ዴሞክራሲ ያላቸው ሀገሮችም «ይሄን ያህል ሰው ሞተ» በማለት የበዛ ኃይል ጥቅም ላይ መዋሉን ይናገራሉ፡፡ እዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት አለ ወይ ? የሚለው አንዱ መነሳት ያለበት ነጥብ ነው፡፡

መጤን ያለበት ግን ጉዳት መቀነስ እየተቻለ ጉዳት የበዛበት አጋጣሚ የለም ማለቴ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዝም ብሎ ከሁኔታዎች ገፊነት የተነሳ ከቁጥጥር ውጪ የሚሆን ነገር አለ፡፡ ሠራዊቱ የሕግ ተገዢነትን (ሩል ኦፍ ኢንጌጅመንት) መመሪያን በኪሱ ይዞ ነው የሚሄደው፡፡ በጥብቅ ያከብረዋል፡፡

ሠራዊቱ ወደ ግዳጅ ከተሰማራ በኋላ እያንዳንዱን ወታደር በርቀት መቆጣጠሪያ (በሪሞት ኮንትሮል) ሳይሆን በአሰራርና በመመሪያ ነው የምትመራው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቀላሉ ሊቆጣጠረው የሚችል ነገር እያለ የሚጠፉ ነገሮች አሉ፡፡ በሁኔታዎች ገዢነት የሚፈጠር ነው፡፡ ተገቢ እንዳልሆነ እናምናለን፡፡ ዳግም በሌላ ግዳጅ አፈጻጸም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ የመቆጣጠር የመከታተል ተጠያቂነትን የማስፈኑ ሥራ የቅርብ ኃላፊዎች ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በድንበር አካባቢ በሚከሰት ግጭት መከላከያ ፈጥኖ ምላሽ አይሰጠም የሚል ወቀሳ ይሰማል፡፡ ሰሞኑን በተለይ በጎንደር ጠረፍ አካባቢ የሱዳኖች ዘልቆ መግባትን በተመለከተ ጉዳዩ ተነስቷል፤ ይሄን እንዴት ያዩታል ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- እንዴት መሰለህ ይሄ ሁኔታ የቆየ ነው፡፡ አንደኛ እስከዛሬ የድንበር ማካለል አልተደረገም፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬዎች የሚያርሱት መሬት አለ፡፡ የሱዳን ገበሬዎች የሚያርሱት መሬት አለ፡፡ ተቀላቅለው ነው የሚኖሩት፡፡ ኬንያ ለምሳሌ ቦረና አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ቦረና አለ፡፡ እዛ ጋ መልካሙ ነገር ድንበሩ ይታወቃል፡፡ በሱዳንና በእኛ በኩል ያለው ድንበር በግልጽ ተሰምሮ አልተካለለም፡፡ ሰው ግን አብሮ ይኖራል፡፡ ሱዳኖች ለኢትዮጵያ ገበሬ መሬት ያከራያሉ፡፡ ሱዳኖቹም ኢትዮጵያውያኖቹም እዛው አብረው የኖሩ ናቸው፡፡ ልክ እንደሌላው ቦታ ሁሉ አንዱ መሬት ያለው ነው፡፡ አንዱ መሬት የሌለው ነው፡፡

የእኛ ወገኖችም ሚሊሺያ አላቸው፡፡ ሱዳኖቹም ሚሊሺያ አላቸው፡፡ በእርሻ መሬት ነው የሚጣሉት፡፡ በሚጣሉበት ጊዜ ሚሊሺያዎቹ ይታኮሳሉ፡፡ ሚሊሺያዎቹ በሚታኮሱበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ የሱዳን ሚሊሺያዎች ጥቃት የደረሰባቸው ሲመስላቸው የሱዳን ወታደሮች ታዘው ሳይሆን በራሳቸው ተነሳሽነት ይደረባሉ፡፡ እኛም እንደዛ ሲሆን ለወገናችን እንደረባለን፡፡ በተረፈ የእኛ መደበኛ ሠራዊት ከሱዳን ሚሊሺያ ጋር የሱዳን መደበኛ ሠራዊትም ከኢትዮጵያ ሚሊሺያ ጋር የሚዋጋበት ምክንያት የለም፡፡ ይሄን ሁለታችንም ማድረግ የለብንም፡፡ አይደረግምም፡፡

አዲስ ዘመን ፡- የኢትዮጵያና የሱዳን መከላከያ ኃላፊዎች ችግሮቹን ለመፍታት ብዙ ጊዜ ሲወያዩ ነበር፡፡ መፍትሄው ምንድነው ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- አዎን እንወያያለን፡፡ ገበሬዎቹ ይረሱ፡፡ ድንበር የመለየቱ ጉዳይ በሁለቱ መንግሥታት በሕግ አግባብ ይጨረስ ነው ሁልጊዜ የምንለው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን የእኛ መከላከያ አልገባም ነው የሚሉኝ? ግጭቱን ማን አስቆመው፤ ሱዳኖቹን ማን መለሳቸው ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- አሁን መጨረሻ ላይ የሆነው አንዳንድ የመደበኛ ሠራዊት አካል የሆኑ ሰዎች መሳተፋቸውን ስላየን ገብተን አቁሙ አልናቸው፡፡ ይሄ ሕገወጥ ነው፡፡ ከስምምነት ውጪ ነው፡፡ አርሶ አደሮቹን ማስታረቅ ነው እንጂ ወደእዚህ ግጭት መግባት የለብንም ነው ያልነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው አሉባልታ ነው፡፡ ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ የሱዳን መደበኛ ሠራዊት ወደ ውጊያ አልገባም፡፡ ቢገባ ደግሞ አርሶ አደሩና ሚሊሺያው ሊያስቆመው አይችልም፡፡ ድንበሩ አካባቢ መቃኘት ሳይሆን ኃይል አለን፡፡ ያ የተወሰነ ኃይል አካባቢውን እየተቆጣጠረ እዚያ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለበላይ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ ሁለቱ ሀገራት ይነጋገራሉ፡፡ በውይይት የሚፈታውን ይፈታሉ፡፡ መስተካከል ያለበት ካለም ለማስተካከል ይረዳል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሀገር ደረጃ ለሁሉም ተቃዋሚ የሰላም ጥሪ ተደርጎአል፡፡ ከሰላም ጥሪው በኋላ የኦነግ ክንፍ በወለጋ አካባቢ መሳሪያ ይዞ ለመንቀሳቀስ መሞከሩ ይነገራል፤ ምን ያህል እውነት ነው ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- የታጠቀ የኦነግ ኃይል ገብቶ እንደዚህ አደረገ የሚለውን በተመለከተ፤ ኦነግ በሚወራለት ደረጃ አይደለም ያለው፡፡ ትርጉም ያለው ኃይል የለውም፡፡ ሰላም ማደፍረስ የሚችሉ የታጠቁ አነስተኛ ሰዎች ግን አሉት፤ ትናንሽ ኃይሎች፡፡ አሁን ለምሳሌ በምዕራብ ወለጋ በኩል በጣም ጥቂት የኦነግ ታጣቂዎች ገቡ፡፡ ከገቡ በኋላ ሰው በገንዘብ ገዙ፡፡ ከህብረተሰባችን መካከል ሥራ የሌለው ቶሎ ይመለመላል፡፡ አነሳስተው ይመለምሉታል፡፡ የገባው ኃይል ላይ ተጨማሪ ያደርጉታል፡፡ ከዛ በኋላ መንገድ መዝጋት ሰው መግደል ይጀምራሉ፡፡ ያለው እውነት ይሄ ነው፡፡ የተወሰኑ ከአንድ የመቶ የማይበልጡ ሰዎች ገቡ፡፡ ሰዎችን መለመሉ 190 ደረሱ፡፡ እነዚህ ደግሞ በቀበሌዎችና በወረዳዎች ተበተኑ፡፡ ሲበተኑ ደግሞ አራት አምስት ሆነው ነው፡፡ በዚያ አካባቢ የተባበራቸውን ሰው እየጨመሩ እያስተባበሩ ቀጣናውን የማወክና የማስፋት ሥራ ነው የሠሩት፡፡

የተደረገው ትክክለኛ ያልሆነ ሥራ ሲሆን፣ የሚወገዝ መወገድም ያለበት ነው፡፡ ጊዜው ለዚህ ዓይነቱ ድርጊት አይመችም፡፡ የሚታይ ሀገራዊ ለውጥ እየመጣ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየለፋና እየደከመ ይገኛል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ያለው ተቀባይነት ከጫፍ ጫፍ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ዓለምም እያወራለት ነው ያለው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ተወካይ ነኝ ብለህ ጫካ ቆይተህ ምንም ውጤት ሳታመጣ ስትቀር፤ ሕዝቡ ታግሎ ባመጣው ለውጥና ውጤት ባለቤት ለመሆን መሞከር ነውር ነው፡፡

አሁን ሕዝቡ እያገለላቸው ነው፡፡ እኛ የታገልነው ለእዚህ አይደለም፡፡ ግቡ ተብላችሁ ሰላም ከሰፈነ በኋላ ምንድነው የምትፈልጉት እያላቸው ነው፡፡ ይሄ የሁለት ሳምንት ግርግር ነው፡፡ እንኳን ዛሬ ድሮ 30 ሺ ተዋጊ ኃይል ይዞ የአልሠራውን ሥራ በአንዴ መጥቶ ለመሥራት መሞከር ምን ማለት ነው፡፡ ትርጉም የለውም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው ሰላም አፋርና ትግራይ ያለው ሠራዊታችን አሁን ባለበት ይቆያል ወይንስ የማንቀሳቀስ ሁኔታ ይኖራል ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- ይሄ የመንግሥት ውሳኔ ነው፡፡ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ተነጋግሮ ሠራዊት እናርቅ ካለ እናርቃለን፡፡ ባለበት ይቆይ ካለ ባለበት ይቆያል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሠራዊቱ የብሔር ብሔረሰብ ተዋጽኦ ተመጣጣኝ አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች ይሰሙ ነበር፤ ይሄንን እንዴት ያዩታል ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- መስመራዊ መኮንንና ከዛ በታች ያለው የብሔር ተዋጽኦ የተጠበቀ ነው፡፡ የተመጣጠነ ነው፡፡ ችግር የለም፡፡ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የብሔር ተዋጽኦውን በተመለከተ ችግር አለ፡፡ ብዙ ጊዜ ተመጣጥኖአል ተብሎ ሲገለጽ ነበር፤ አልተመጣጠነም፡፡ የግድ ለማመጣጠን ሪፎርም መካሄድ አለበት፡፡

አዲስ ዘመን ፡- አሁን ይሄ እየተሠራ ነወይ ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- እየተሠራ ነው፡፡ በየደረጃው ይሠራል፡፡

አዲስ ዘመን ፡- እስከታች ይወርዳል ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- በታችኛውማ ደረጃ ምንም ችግር የለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከየት ጀምሮ ነው አለመመጣጠኑ ጎልቶ የሚታየው ?

ጄኔራል ብርሃኑ ፡- ከክፍለ ጦር በላይ ያለመመጣጠን አለ፡፡ ይሄ ማለት ግን ተሳትፎ የለም ማለት አይደለም፡፡ ተሳትፎ አለ፡፡ መመጣጠኑ የሀገሪቱን ገጽታ በሚያሳይ ልክ አይደለም፡፡ ይሄ መሠራት መስተካከል አለበት፡፡ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የሚመስል ሠራዊት ነው መገንባት ያለበት፡፡ ከታች ብዙ ኃይል እየመጣ ነው፡፡ በዛ መልክ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ እላይ ያለው የማመጣጠን ሥራ ዘግይቶአል፡፡ ችግሩ የተለያየ የራሱ ምክንያቶች አሉት፡፡ አንደኛው ከሌላው መምጣት ያለበትን ኃይል በበቂ ያለማዘጋጀት ነው፡፡፡እያንዳንዱ ለማመጣጠን መቀነስን ነው የሚያስበው፡፡ ሳትቀንስ ግን ማመጣጠን ትችላለህ፡፡ ሳትቀንስ የማመጣጠን ሥራ በደንብ ሠርተናል ማለት አይቻልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሠራዊቱ ታማኝነቱ ለሀገሪቷና ለሕዝቧ ሁኖ ያለ ተጽእኖና እንዲቀጥል፤ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ጠንካራ ግንዛቤ እንዲፈጠር የሚሰራ ስራ አለ ?

ጄኔራል ብርሃኑ ፡- አሁን ሕገ መንግሥቱን ስለሸረሸርነው ነው እንጂ ሕገ መንግሥቱ እኮ ስለ ኢትዮጵያ ነው የሚያወራው፡፡ ሠራዊታችን የሚያወራው ስለ ኢትዮጵያና ስለ ሕገመንግሥቱ ነው፡፡ቋንቋውም ይሄ ነው፡፡ ይህንን በአዋጆች፣ በደንቦችና በመመሪያዎች ወደ መሬት ማውረድ ያለበት ፖለቲካዊ አመራሩ መሆን ነበረበት፡፡ ፖለቲካዊ አመራሩ ደግሞ ይሄን በደንብ እየመራው አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ነው ኢሕአዴግ ችግር ውስጥ የገባው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ኢትዮጵያን እጠብቃለሁ እንጂ የሆነ ፓርቲ እጠብቃለሁ አይልም፡፡ ሠራዊቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መኖር እንዳለበትና የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር በምርጫ መሆን እንዳለበት ያምናል፡፡ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ይሠራል፡፡ ለዚህ ነው የዓላማ ብዥታ ችግር ሠራዊቱ የለበትም ያልኩህ፡፡

ሕገመንግሥቱ በተጻፈበት መንገድ ፖለቲካዊ አመራሩ ሰርቶአል ወይ የሚለው ነው ጥያቄ እያስነሳ ያለው፡፡ አልሠራችሁም ብሎ ሕዝቡ አመጸ፡፡ የፖለቲካ አመራሩ ሕዝቡ እያነሳ ያለው ጥያቄና ተቃውሞ እውነት መሆኑን አምኖ ተቀበለ፡፡ የእኔ ችግር ነው አለ፡፡ አሁን ችግሩን የማስተካከል ሥራ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ሠራዊቱ ይሄንን መደገፍ አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመከላከያ ስር የሚገኙ የተለያዩ የልማት ተቋሞች ለአገሪቱ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል ?

ጄኔራል ብርሃኑ ፡- የመከላከያው ኢንዱስትሪ እና ሌሎች የመንግሥት ኢንዱስትሪዎች የነበሩት በአንድ ዕዝ ስር ሆነው በሜቴክ እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡ የመከላከያን ፍላጎት እንዲያሟላ እንዲሁም አጠቃላይ የሀገሪቱን ኢንዱስትሪ እንዲመራ ተብሎ ነበር የተቋቋመው፡፡ ለሲቪልና ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን ሲያመርቱ ነበር፡፡ የእንደነዚህ አይነት ተቋማት ዕድገት ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ባሳለፍነው ጊዜ መጠን ተራምደናል ወይ የሚለውን መገምገም አለብን፡፡ ጅምሩ ጥሩ ነበር፡፡ በመሀል ትንሽ ተቋሙ ላይ ያለመርካት ሁኔታ በተለያዩ ኃይሎችም ነበር፡፡ ቢሆንም አሁን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን ፡- ብዙ ዓመታት አገልግለው ጡረታ ሳያገኙ የተሰናበቱ በከፋ ችግር ላይ ያሉ የቀድሞው ሠራዊት አባላት በመላው ሀገሪቱ አሉ፡፡ ጡረታ ሲጠይቁ የግል ማህደራችሁ የለም አልተገኘም ነው መልሱ፡፡ ምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያና ጡረታ ሚኒስቴር በመመላለስ የኖሩም አሉ፡፡ ወታደሮች፣ የበታች ሹሞችና መኮንኖች የነበሩ በተለያየ ክስ የጡረታ መብታቸውን ለረዥም ዓመታት የተነፈጉ ዜጎችም አሉ፡፡ ይህ ችግር እንዴት ይፈታል ?

ጄኔራል ብርሃኑ፡- የጡረታ መብታቸው እንዲከበር እየተሠራ ነው፡፡ ጡረታቸው ሳይከበር የወጡ ሰዎች በጥፋት የተከሰሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ በአለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአንዳንዶች ማዕረጋቸው በክብር እንዲመለስ ጡረታቸውም እንዲከበር ካስደረጉ በኋላ በዚሁ መነሻነት በእነሱ ብቻ ሳይቆም ጡረታቸው ሳይከበር የተሰናበቱ የቀድሞው የሠራዊት አባላት በሙሉ ማሕደራቸው ተፈልጎ ታውቀውና ተለይተው መከላከያ ሚኒስቴር ውሳኔ ሰጥቶ ጡረታቸው እንዲከበር እየሠራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን!

ጄኔራል ብርሃኑ ፡- እኔም አመሰግናለሁ !

Source – ethiopress. gov.t media Addis Zemen