ቁስልን መጫር፣ ጭሮ መቧጨር፣ ቧጭሮ ማቁሰል፣ አቁስሎ ማመርቀዝ እና አመርቅዞ እንዳይድን ማድረግ የታሪክ አላማ አይደለም፤ ታዬ ቦጋለ

[addtoany]
‹‹ ቁስልን ማመርቀዝ እና አመርቅዞ እንዳይድን ማድረግ የታሪክ አላማ አይደለም ›› የታሪክ መምህር እና ደራሲ ታዬ ቦጋለ
(ኢፕድ) :- ቁስልን መጫር፣ ጭሮ መቧጨር፣ ቧጭሮ ማቁሰል፣ አቁስሎ ማመርቀዝ እና አመርቅዞ እንዳይድን ማድረግ የታሪክ አላማ አይደለም ሲሉ የታሪክ መምህር እና ደራሲ ታዬ ቦጋለ ገለጹ። ህወሓት/ ትህነግ ስልጣን ዘመኑን ለማርዘም አማራና ኦሮሞን እንደማህበረሰብ ማጋጨትን እንደ አንድ ስልት አድርጎ ይዞት እንደነበረም አስታወቁ ።
የታሪክ መምህር እና ደራሲ ታዬ ቦጋለ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ቁስልን መጫር፣ ጭሮ መቧጨር፣ ቧጭሮ ማቁሰል፣ አቁስሎ ማመርቀዝ እና አመርቅዞ እንዳይድን ማድረግ የታሪክ አላማ አይደለም፤ የታሪክ ትርክቶች ከታሪክ ዓላማ ውጪ ከሆኑ የታሪክ ትርክቶች ሳይሆኑ የፖለቲካ ፈጠራ ናቸው ብለዋል።
የፖለቲካ ፈጠራ የታሪክ ትርክቶቹ መነሻቸው አገር ማፍረስ እና በማህበረሰብ መካከል ግጭት መፍጠር እንጂ ለአሁኑ ትውልድ ዳቦ አይሆኑም ያሉት አቶ ታዬ ቦጋለ፤ የታሪክ ትምህርት ዓላማው ያለፈውን ለማጥራት፣ ዛሬን በጥሩ መሰረት ላይ ለማነጽ እና ነገን በብሩህ ሁኔታ ለመገንባት መሆኑንም ተናግረዋል።
“ህወሓት/ ትህነግ ሲቋቋም በጥቂቶች የተመሰረተው ቡድን ነው። ይሄ ስርዓት ውስብስብ ባህሪያት ያሉት ነው። በፖለቲካ ቋንቋ መግለጽ ያስቸግራል። አንደኛው መለስ ዜናዊ በነበረበት ረጅም ጊዜ በአንድ በኩል ሞኖክራሲ ነበር። ሞኖክራሲ ማለት የአንድ ሰው አምባገነን አገዛዝ ነው። የኢኮኖሚ ባህሪያቱን ስንመለከት ደግሞ አሪስቶክራሲ (ኦሊጋርኪ) ነው። የጥቂቶች የበላይነት የሚንጸባረቅበት ስርዓት ነው። ይሄ ስርዓት በባህሪው መቆየት እንደማይችል፣ አምባገነን እንደሆነ፣ በፍርሃት የተከበበ ስሜት ይዞ ስለተነሳ እንዲቆም አማራና ኦሮሞን እንደማህበረሰብ ማጋጨትን አንድ ስልት አድርጎ ይዞ ነበር” ብለዋል ።
አማራውን ትምክህተኛ፣ ኦሮሞን ጠባብ፣ ደቡቡን የስብዕና መሸርሸር ያለበት፣ አርብቶ አደር አካባቢ፤ ሱማሌ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪን ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ለመሸከም የሚያስችል ቁመና የሌላቸው አጋር ሆነው የሚቀጥሉ በማድረግ ስርዓቱ እንዲቀጥል ማድረጉን አመልክተዋል።