በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር በዓበይት ጉዳዮች ላይ በመስማማት መጠናቀቁ ታወቀ

[addtoany]
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር በዓበይት ጉዳዮች ላይ በመስማማት መጠናቀቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታወቀ

Imageበታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት እና ዓመታዊ የሥራ ክንውን ላይ ያተኮረውና ካለፈው የቀጠለው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ልዩ ስብሰባ ሐምሌ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የሚያደርጉትን ድርድር አጀንዳው ባደረገው ስብሰባ፣ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር በሆኑት ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ ሰብሳቢነት መካሄዱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሦስቱ ሀገራት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዲችሉ የአፍሪካ ኅብረት ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎችን የማበጀት ሥራ አስቀድሞ በነበሩ ቀጣናዊ መፍትሔ ሰጪ አሠራሮች አማካኝነት መከወኑንም አድንቀዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ግብጽ እና ሱዳንን ፈጽሞ በማይጎዳ መልኩ፣ የአባይን ውኃ ፍትሐዊነት በተሞላበት እና ለሁሉም ተደራሽ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ኢትዮጵያ ባላት ውሳኔ እንደምትጸና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
Imageበቀጣናው የታየው ወቅታዊ የዝናብ እና የፈሰስ መጠን መጨመር ግድቡን ለመሙላት ሁኔታዎችን አመቺ አድርጓል ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጸ/ቤት መግለጫ ፣የግድቡን የመጀመሪያ የውኃ ሙሌት እና ዓመታዊ የሥራ ክንውን አስመልክቶ፣ ኢትዮጵያ ሚዛናዊ እና ሦስቱም ሀገራት በፍትሐዊነት ከ ዓባይ ወንዝ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ድርድርን ለማካሄድ ባላት አቋም ትቀጥላለች ብሏል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከተገኘው ከፍተኛ የዝናብ መጠን የተነሣም፣ የግድቡ የመጀመሪያ ዓመት የውኃ ሙሌት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ውኃው በግንባታ ላይ ያለውን ግድብ አልፎ መፍሰስ መጀመሩን መግለጫው አመልክቷል፡፡
በሀገር መሪዎች እና ርዕሳነ መንግሥታት ደረጃ የተካሄደውን ስብሰባ፣ ሁሉም አካላት በዓበይት ጉዳዮች ላይ በመስማማት ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ድርድሩ በስምምነት እንዲቋጭ መንገድ ጠርጓል። በዚህም መሠረት፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የውኃ ሙሌቱን የተመለከቱ የቴክኒክ ውይይቶች በአፍሪካ ኅብረት በኩል በሚደረገው ሂደት እንዲቀጥሉ እና ወደ አጠቃላይ ስምምነት እንዲደረስ ተስማምተዋል።