በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ውሃ መያዝ አትችልም ከተባለ የሚፈጠረው ነገር የግድቡን ሥራ ማቆም ነው – የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ

የህዳሴ ግድብ ቅድመ ኃይል ማመንጫ የሁለት ጀነሬተር ተርባይን ሥራዎች ተጠናቅቆ በኮንክሪት እየተሞሉ ነው- ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ
(ኢፕድ) : ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ የተከናወኑ ሥራዎች ሲመዘኑ በ2012 ዓ.ም የላቀ ሥራ መሰራቱን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ አስታወቁ።የግድቡ ግንባታ በሁሉም መስክ የተሳካ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የግድቡ ሥራ አስኪያጁ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅም በሁሉም አቅጣጫ በሶስት ሽፍት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ የግድቡ የሲቪል ኢንጅነሪንግ ሥራው 87 በመቶ፣ የብረታ ብረት ሥራዎቹ ደግሞ ከ31 በመቶ በላይ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል የተርባይንና የጀነሬተር ሥራዎች አፈጻጸምም 45 በመቶ እንደሚገኝ ታናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ችግር የነበረባቸው የቅድመ ኃይል ማመንጫ የብረታ ብረት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተነስተው በአዲስ መተካታቸውን ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ፣ የግድቡ የግርጌ የውሃ ማስተንፈሻ (የቦተም አውትሌት) እንዲሁም ከቅድመ ኃይል ማመንጨት ጋር የተገናኙ የሁለት ጀነሬተር ተርባይን ሥራዎች ተጠናቅቆ በኮንክሪት እየተሞሉ መሆኑን አብራርተዋል።
የ11 ቀሪ ዩኒቶች የብረታ ብረት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነና ሌሎች ለሲቪል ኮንትራክተሮች የተሰጡ ሥራዎች ደግሞ በቅርቡ እንደሚጀመሩ አስታውቀዋል።
ለሁለቱ ቅድመ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚሆን የብረታ ብረት ሥራዎች ተከናውነው ኮንክሪት እየተሞሉ መሆኑን የጠቆሙት ሥራአስኪያጁ፣ በቀጣይም የጀነሬተር ተርባይን ተከላ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
በግድቡ በተለይም የመካከለኛው ውሃ ይፈስበት የነበረው ቦታ ርዝመቱ 525 ሜትር የነበረ ሲሆን፣ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ 560 ሜትር ለማድረስ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ጎንና ጎኖቹም በኮንክሪት እየተሞሉ መሆኑን አስታውቀዋል። የግድቡ ሥራ ከተጀመረ አንስቶ እንደዚህ ዓመት በሁሉም አቅጣጫ በሙሉ አቅም የተሰራበት ጊዜ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ በሁሉም መስክ የተሳካ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመለከቱት ኢንጅነር ክፍሌ፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካሉም፣ በሲቪሉም፣ በብረታ ብረት ሥራውም በሶስት ሽፍት ያለ እረፍት እየተሰራ ነው፤ ይህም በጣም አስደሳችና እስከ ዛሬ ያልተሰራበት አካሄድ ነው ብለዋል።
“በዚህ ዓመት ውሃ ሙሌቱ ይጀመራል ስላልን ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ያለው የግድቡ ሥራ አፈጻጸም በራሱ የውሃ ሙሌት እንዲጀመር አስገዳጅ ነው” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ “የመካከለኛውን የግድቡን ክፍል ከ525 ወደ 560 ሜትር ከፍ እያደረግን ስለምንሄድ ውሃ ሙሌቱ ያስፈልጋል፤ በዚህም 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ሜትር ኩዩብ ውሃ እንይዛለን። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሁሉም ነገር ተስተካክሎልን ከሰራን ወደ 590 ሜትር ስለምናደርሰው ውሃ የመያዝ አቅማችን 16 ነጥብ 5 ሜትር ኩዩብ ይሆናል” ብለዋል።
ሥራ አስኪያጁ “በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ውሃ መያዝ አትችልም ከተባለ የሚፈጠረው ነገር የግድቡን ሥራ ማቆም ነው፤ ምክንያቱም 560 ሜትር ከተደረሰ በኋላ ስትራክቸሩ በጣም ትልቅ በመሆኑ ግንባታው በምንና እንዴት እንደሚነሳ ማሰብ ይከብዳል፤ ከዚህ አንጻር የውሃውን ሙሌት የሚያመጣው የሥራው አስገዳጅነት ነው” ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም አሁን ላይ 74 በመቶ ደርሷልም ነው የተባለው።