የግብፅ የእኔ ጥቅም ብቻ ይጠበቅ አቋም ድርድሩን እየተፈታተነ ነው – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

የግብፅ የአባይን ውሃ ብቻዬን ልጠቀም ግትር አቋም ደግም ለተጀመረው ድርድር እንቅፋት ሆኗል – አቶ ገዱ
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ሰሞኑን እየተካሄደ ያለውን የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር አስመልክተው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
(ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብፅ የአባይን ውሃ ብቻዬን ልጠቀም ግትር አቋም ደግም ለተጀመረው ድርድር እንቅፋት መሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገለፁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አምስተኛ ቀኑን በያዘው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የሶስትዮሽ ድርድር የእስካሁን ውጤት ላይ እየሰጡት ባለው መግለጫ የግብፅ የእኔ ጥቅም ብቻ ይጠበቅ አቋም ድርድሩን እየተፈታተነ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፥ ግብፅ በድርድሩ በተለመደው ሁለት አካሄዷ ቀጥላበታለች ነው ያሉት። ግብፅ አንድ እግሯን ድርድሩ ላይ አንድ እግራን የፀጥታው ምክር ቤት አስቀምጣ መደራደርን መምረጧን በማንሳት።
በድርድሩ ግብፃውያኑ የፈለጉት እና የጠየቁት ሁሉ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ የሚሰጡት ግን የላቸውም ነው ያሉት።
ግብፅ የጋራ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ኢትዮጵያ ውሃ መሙላት አትችልም የሚል ተቀባይነት የሌለው ሃሳብ ይዛ መቀጠሏም ተነግራል።ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመግለጫቸው እንዳመላከቱት ግብጽ ከዚህ በፊት በድርድሩ ስታሳየው የነበረውን ሙሉ የዓባይ ውኃ ይገባኛል አካሄድ አሁንም እየተከተለች ነው፡፡በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመናት የተከተሉት ይህ አካሄድ ለአሁኑ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን በምንም መልኩ የማያስኬድና የማንቀበለው ነው ብለዋል አቶ ገዱ በመግለጫቸው፡፡

ግብጽ አሁንም ፍላጎቷ ድርድሩ እንዲቋረጥ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት በ2015 (እ.አ.አ) ከነበረው የመርህ ስምምነት ውጭ ሌላ መተሳሰሪያ የሌለን በመሆኑ ግብጽ ድርድሩን አቋርጣ የምትወጣ ከሆነ ከዚህ በኋላ ለድርድር የምንቀመጥበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡እየተደራደርን ያለነው ሁሌም እኔ ብቻ ልጠቀም ከምትለው፣ እድሜ ልኳን የኢትዮጵያን ጥቅም ከምትጻረረው፣ ሀገራችን ዘላቂ ጥንካሬ እንዳይኖራት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከምትሠራው ግብጽ ጋር ነው ሲሉም አቶ ገዱ የግብጽን አቋም አስረድተዋል፡፡

የግብጽ ሕዝብ መንግሥታቸው ምክንያታዊና ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ ተመስርቶ እንዲደራደር ጫና እንዲያሳድሩም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡