የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምላሽ ሰጥቷል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተፈጽመዋል ብሎ ከሰሞኑ ያወጣው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሪፖርት ሚዛኑን ያልጠበቀና በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ያልተገነዘበ ነው በማለት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ሰጥቷል።

ሚኒስቴሩ በሰጠው ምላሽ ላይ እንዳለው “ሪፖርቱ በጥቅሉ በአገሪቱ ለውጥ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ሰፊውን ፖለቲካዊና የጸጥታ ሁኔታ ከግንዛቤ ያላስገባ እንዲሁም ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ቁንጽል የጸጥታ ሁኔታ ትንተና ነው” ሲል ተችቶታል።

ጨምሮም የኢትዮጵያ መንግሥት የአንድም ሰው ህይወት መጥፋት የማይፈቅድ መሆኑን ገልጾ፤ እነዚህ በሪፖርቱ ላይ የቀረቡት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመው ከሆነ መንግሥት ገለልተኛ የሆነ ማጣራት እንዲካሄድ ያደርጋልም ብሏል።

በሪፖርቱ ላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ሰፊና ስኬታማ ሠላም የማስፈን ጥረቶችን ሆን ተብለው መታለፋቸውን አመልክቶ እነዚህ ሠላም የማስፈን ጥረቶች በአካባቢዎቹ ሕብረተሰቦች፣ በክልል እንዲሁም በፌደራል መንግሥት አካላት የተቀናጀ ድጋፍ አማካይነት ሐይማኖታዊና ባሕላዊ መሪዎችን እንዲሁም ሲቪል ማኅበረሰቡን ባሳተፈ ሁኔታ መከናወኑን አመልክቷል።

በሪፖርቱ ላይ በተጠቀሱት ስፍራዎች ሕግና ሥርዓትን በማስከበር በኩል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የጸጥታ አካላት በገለልተኛ ወገኖች ሳይቀር ምስጋናን እንዳገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ጠቅሶ መንግሥት “በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ግጭቶችን የመፍቻ መንገዶችን በመጠቀም በሰላማዊ ሁኔታ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ያደረገውን ጥረት ሪፖርቱ ከግንዛቤ አላስገባም” ሲል ወቅሷል።

በተጨማሪም የጸጥታው አካል ከልማትና ከሰብአዊ ተቋማት ጋር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ክብራቸው ተጠብቆ በፈቃዳቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን መግለጫው አስታውሶ ሪፖርቱ ግን እንዳላየው አመልከቷል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያቤቱ ምላሽ እንዳለው በሪፖርቱ ላይ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚያጋጥሙ ግጭቶች በአብዛኛው መፍትሄ እንዳገኙ ጠቅሶ “በአገሪቱ የፖለቲካው መድረክ በስፋት ተከፍቷል የተጠቀሱት የጸጥታ ችግሮች በአብዛኛው ግጭቶች ሳይሆኑ የሽፍትነት ድርጊቶች ናቸው” ብሏል።

በአምነስቲ ሪፖርት ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ክልሎች ሰፊ ከመሆናቸው በተጨማሪ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሂደት የተጀመሩባቸው ቦታዎች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በእነዚህ ክልሎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሉን መግለጫው አክሎ ገልጿል።

መግለጫው በማጠቃለያው ላይ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝቡን አንድነት በተለያዩ መስኮች በማጠናከር የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን በመግታት የዜጎችን ህይወት ለማመታደግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ፤ “ጊዜያዊ የፕሮፓጋንዳ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ወረርሽኙ የደቀነውን ከባድ አደጋና ተጽዕኖ ችላ በማለት በድርጅቱ የወጣው ሪፖርት ከመርህ የራቀና ግዴለሽነት የታየበት ነው” ሲል ወቅሷል።

የመብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ልዩ ልዩ መንግሥታዊ የፀጥታ ኃይሎች እና ከእነርሱ ጋር በትብብር የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኢመደበኛ ቡድኖች አሰቃቂ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅመዋል ሲል ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።

ድርጅቱ ይፋ ባደረገው የሰባ ሁለት ገፅ ጥናታዊ ዘገባው ለአንድ ዓመት ያህል በሁለቱ ክልሎች አደረኩ ባለው ምርመራ በኦሮሚያ ምሥራቅ እና ምዕራብ ጉጂ እንዲሁም በአማራ ምዕራብ እና መካከለኛ ጎንደር ዞኖች የመከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ፖሊስ፣ የየአጥቢያ ባለስልጣናት እና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው የወጣት ቡድኖች አባላት ግድያን ጨምሮ የመብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ሲል ከሷል።

“ከሕግ ማስከበር ባሻገር፣ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች የተፈፀሙ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በፀጥታ ኃይሎች የሚፈፀሙ ህገወጥ ግድያዎች፣ የጅምላ እስሮች፣ በግዳጅ ማፈናቀል እና የንብረት ማውደሞች በአፋጣኝ መቆም እንዳለባቸው በይፋ ትዕዛዝ እንዲሰጡ ጠይቋል።