የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የቀረበለትን የሕገ መንግስት የትርጉም ጥያቄ ምላሽ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቀረበ።

(ኢፕድ) የኢፌዴሪ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ምርጫን በወቅቱ ማካሄድ ባለመቻሉ እንዲሁም የምክር ቤቶቹን እና የአስፈፃሚ አካላትን የስራ ዘመን አስመልክቶ የቀረበለትን የሕገ መንግስት የትርጉም ጥያቄ ምላሽ ትናንት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቀረበ።
ጉባኤው ከምክር ቤቱ ጥያቄው ከቀረበለት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አንፃር መመርመሩን አመልክቶ ፣ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ ከመስጠቱ በፊት በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀፅ 9 መሰረት በሕገ መንግስት የትምህርት ዘርፍ የተሰማሩና ልምዱ ያላቸውን ባለሙያዎች፣ ሕገ መንግስቱን በማርቀቅ ሂደት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ ያላቸውን ግለሰቦች፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ተቋማት ለሕብረተሰቡ ግልፅ በሆነ መንገድ በተለያዩ ሚዲያዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በማስተላለፍ በጉባኤውም ሆነ በሀገሪቱ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን የመስማት ሂደት ማከናወኑን አስታውቋል።
ከመስማት ሂደቱ ጎን ለጎን ጉባኤው ባደረገው ጥሪ መሰረት በፅሁፍ የቀረቡ በርካታ ሃሳቦችን እንደተመለከተ አመልክቷል ።
በተጨማሪም ሃሳብ ለማጎልበት የሚረዱ ጥናቶችን በጉባኤው ፅህፈት ቤት ባለሙያዎች ማስጠናቱን ገልጾ ፤ እነዚህን መሰረት አድርጎ ጉባኤው ባስቀመጣቸው ዋና ዋና ጭብጦች ላይ ለሁለት ሳምንታት ያህል ተከታታይና ጥልቅ የሆነ ውይይት በማድረግ ምላሽ በማዘጋጀት የውሳኔ ሃሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን ገልጿል።