67 በመቶ የሚሆኑት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆኑ፣ ቫይረሱ በማኅበረሰቡ መካከል መዛመቱን ያሳያል ተባለ

ኮቪድ19ን ለመከላከል የተቋቋመውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰብሳቢነት ሥራውን የሚከውነው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ዛሬ ጠዋት ስብሰባ አካሂዷል፡፡ እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ የክንውን ሂደቱም ተገምግሟል፡፡

የጤና ሚኒስቴር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ገልጿል፡፡ 67 በመቶ የሚሆኑት አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆኑ፣ ቫይረሱ በማኅበረሰቡ መካከል መዛመቱን እንደሚያሳይም ተመላክቷል፡፡ ቤት ለቤት የሚካሄደው የሙቀት ልኬት እና የቫይረሱን ምልክቶች የመለየት ሥራ እንዳለ ሆኖ፣ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ የመኖሩን ሂደት የሚፈትሹ ከ700 የሚበልጡ ቡድኖች በመላው ሀገሪቱ ተሠማርተዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ንዑስ ኮሚቴ እንዳስታወቀው፣ የመንግሥት ተቋማት በአካል ተገናኝተው በሚያካሂዷቸው ስብሰባዎች ምትክ የሚከናወኑ በቴክኖሎጂ የታገዙ ስብሰባዎች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ ነው፡፡ በ11 ተቋማት ውስጥ ለወትሮው ገጽ ለገጽ የሚሰጡ 75 መንግሥታዊ የሆኑ አገልግሎቶችም፣ አሁን በኢንተርኔት በመታገዝ እየተካሄዱ ነው፡፡ በተመሳሳይ፣ ሌሎቹም ንዑሳን ኮሚቴዎች ዋና ዋና ክንውኖችን እንዲሁም ተግዳሮቶችን የገለጹ ሲሆን፣ በተለይም በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ትኩረት ተደርጎበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመላው ሀገሪቱ የምርመራ ዐቅም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ወረርሽኙን ከመመከት ጎን ለጎን፣ በዐበይት ዘርፎች ምርታማነትን ማስቀጠል እጅግ አስፈላጊ እንደ ሆነም ተናግረዋል፡፡

Source – Office of the Prime Minister-Ethiopia