በፀጥታ ኃይሎች በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች 140 ሰዎች ተገድለዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል

የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ዘግናኝ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈፅመዋል ሲል አመለከተ።

DW : ድርጅቱ ዛሬ ይፋ ባደረገው ሰፋ ያለ መግለጫውን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ፀጥታን ለማስከበር በተካሄዱ ዘመቻዎች አስገድዶ መድፈር፣ የዘፈቀደ እስር፣ ከሕግ አግባብ ውጪ ርምጃዎች መውሰድ እና ቤቶች ማቃጠል ተፈጽሟል ብሏል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት እንደሚለው፤ በተጠቀሱት ሁለት ክልሎች ውስጥ በዚህ ዘመቻ ቢያንስ 140 ሰዎች ተገድለዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።

ከጎርጎሪዮሳዊው 2018 ታኅሣስ እስከ 2019 ታኅሣስ ወር ያሉትን ጊዜያት በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ይዞታውን በቃኘበት ዘገባው ምንም እንኳን ሺህዎችን ከእስር የመልቀቅ፣ ሲቪክና ፖለቲካዊ ምሕዳሩን የማስፋት እንዲሁም ጨቋኝ ሕጎችን የማሻሻል ሂደቶች ቢኖሩም የፀጥታ ኃይሎች አስከፊ የሰብያዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን አመልክቷል።

የድርጅቱ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪቃ ዳይሬክተር ዲፕሮስ ሙቻና፤ «የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሀገሪቱን ጥቁር የሰብዓዊ መብቶች ሪከርድ ለማሻሻል ትርጉም ያላቸው መሻሻሎችን ቢያደርጉም የፀጥታ ኃይላት ያለምንም ተጠያቂነት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዲፈጽሙ መፍቀዱ ተቀባይነት የለውም።» ብለዋል። አክለውም፤ ምርጫ በቅርብ ርቀት በሚታሰብበት በዚህ ወቅትም መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሥራቸውን በሕግ አግባብና ያለአድልዎ እንዲያከናውኑ ለማድረግ አፋጣኝ ርምጃ ካልወሰደ በቀር ጥቃትና ወከባው ተባብሶ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን እንደሚችልም አሳስበዋል።