የሕዳሴው ግድብ ውኃ የሚተኛበት አንድ ሺ ሄክታር የደን ምንጣሮ ሥራ ሊጀመር ነው

የሕዳሴው ግድብ ውኃ የሚያርፍበት የደን ምንጣሮ ሊጀመር ነው
. በሄክታር 29 ሺ ብር ወጪ ይደረጋል
. ከሁለት ሺ በላይ ለሚሆኑ የክልሉ ወጣቶች የስራ ዕድል ይፈጥራል
(ኢፕድ) – የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት በመጪው ሐምሌ ውሃ ሙሊት የሚጀምር በመሆኑ ውኃ የሚተኛበት አንድ ሺ ሄክታር የደን ምንጣሮ ሥራ በመጪው ሰኞ ግንቦት 24 እንደሚጀመር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት አጀንሲ አስታወቀ።ለምንጣሮውም በአንድ ሄክታር 29 ሺ ብር ወጪ ይደረጋል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፣ ከዚህ በፊት በተከናወኑት የታላቁ የሕዳሴው ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የደን ምንጣሮ ሥራዎች የክልሉ ሥራ አጥ ወጣቶች እምብዛም ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ገልጸው በዚህ ዓመት የሚከናወነውን የደን ምንጣሮ ሥራ በክልሉ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዲከናውኑ መደረጉ የሚያስመሰግን ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ኃላፊነትን የሚጠይቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት መያዝ የሚጀመረው ውኃ የሚተኛበት አንድ ሺ ሄክታር ቦታ ለምንጣሮ መዘጋጀቱን የተናገሩት አቶ በሽር ለዚህ ሥራም በ70 ማህበራት የተደራጁ አንድ ሺ ሁለት መቶ ወጣቶችና በሥራቸው ከ800 በላይ ወጣቶች (በድምሩ ከሁለት ሺ በላይ የሚሆኑ የክልሉ ሥራ አጥ ወጣቶች) በ45 ቀናት ሥራውን ለማጠናቀቅ ከሚመለከተው አካል ጋር ውል ማሰራቸውን ተናግረዋል።
በሥራው ላይ የሚሰማሩ ወጣቶች መመንጠር፣ መከትከትና ለከሰል ዝግጁ ማድረግ፣ ወደ ተዘጋጀለት ቦታ ማጓጓዝ፣ ወለል አድርጎ ማጽዳት(ማዘጋጀት) እና ሌሎች በውላቸው የተጠቀሱ አስፈላጊ ሥራዎችን ጨምሮ በማከናወን በአንድ ሄክታር 29 ሺ ብር ክፍያ እንደሚፈጸምላቸው አብራርተዋል።
በሥራ ዕድሉ በክልሉ የሚገኙ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ሥራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንና በግድቡ አቅራቢያ ከሚገኙ ሰባት ወረዳዎች የተደራጁ ሥራአጥ ወጣቶች የሥራውን 40 በመቶ እንዲያከናውኑ፣ ቀሪውን 60 በመቶ ደግሞ ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ተደራጅተው ለመጡ ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራው ተከፋፍሎ መሰጠቱን አስረድተዋል።
በሥራው ላይ የሚሰማሩት ወጣቶች ከኮሮና ወረርሽኝም ሆነ ከሌሎች በሽታዎች ጤናቸውና ደሕንነታቸው ተጠብቆ ሥራውን በሚፈለገው መንገድ፣ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ፣ በሚፈለገው ጥራት እንዲያከናውኑ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በቅርበት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚሰጥ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ ወደሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
«ታላቁ የህዳሴ ግድብ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ካለው ጥሪት ላይ እየቀነሰ እየገነባ ያለው ግድብ ነው።ባናተርፍም በዚህ የሚያኮራና የሞት የሽረት በሆነው አገራዊ ተግባር ላይ መሳተፋችን የገንዘብ ጉዳይ ሳይሆን የዜግነት ጉዳይ አድርገን በማየት በሙሉ ቁርጠኝነት ሰርተን በተቀመጠው ጊዜ እናስረክባለን» ሲሉ በሥራው ላይ የሚሰማሩት የተደራጁ ወጣቶች በወረዳ ደረጃ ሁሉንም በአካል አግኝተው ባወያዩበት ወቅት መናገራቸውን አቶ በሽር ገልጸዋል።
አቶ በሽር በገለጻቸው በክልሉ ተደራጅተው ሥራውን ለማከናወን በሚጠባበቁት ሥራ አጥ ወጣቶች እና ለዚህ ዓመት ለምንጣሮ ዝግጁ የተደረገው ቦታ የሚመጣጠን አይደለም።በመሆኑም የአሁኑ ሥራውን ለመጀመር ወጣቶቹ ጉልበታቸውን ብቻ ይዘው ወደሥራው የሚሰማሩበት ነው።በቀጣይ በሥራው ላይ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ወጣቶች ተሳታፊ ይሆናሉ። በመሆኑም በቀጣይ በሥራው ከሚያገኙት ገቢ 30 በመቶ በመቆጠብ በሌሎች ሥራዎች ላይ የሚሳተፉባቸው ዕድሎች ሰፊ መሆናቸውን አብራርተዋል።