ግብጽ ወደ ድርድሩ ተመለሰች አልተመለሰች ከሚለው ይልቅ ኢትዮጵያ የቤት ሥራዎቿን በመሥራት ላይ ማተኮር አለባት

ግብጽ ወደ ድርድሩ ተመለሰች አልተመለች ከሚለው ይልቅ ኢትዮጵያ የቤት ሥራዎቿን በመሥራት ላይ ማተኮር አለባት
. የግድቡ ግንባታ እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር የመደራደሪያ አቅምም እየጎለበተ ይሄዳል- የፖሊሲ ጉዳዮች ተመራማሪው ዶክተር ግርማ ተሾመ
**
(ኢፕድ) – በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ሂደት ላይ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር ተቋርጦ የነበረውን ድርድር ዳግም ለመቀጠል ግብጽ መስማማቷን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አማካኝነት በቅርቡ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
የሦስትዮሽ ድርድሩ በተጀመረበት ሂደት እንዳይከናወን የተለያዩ ተግዳሮቶችን በመፍጠር በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መንገዶች ጫና ለማሳደር ስትጥር የከረመችው ግብጽ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር ተቋርጦ የነበረውን ድርድር ለመቀጠል መስማማቷን ይህንንም ይፋ ማድረጓ በብዙዎች ዘንድ ግርታን ፈጥሯል። ግብጽ በቀጣይ ጊዜያት በሚደረጉ ድርድሮችና ውይይቶች ለመሳተፍ ፈቃደኝነቷን የገለፀችው ከስምምነት ለመድረስ ወይስ እንደተለመደው ለሌላ ተግዳሮት ጊዜ ለመግዛት የሚል ጥያቄ ብዙዎች እያነሱ ነው።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስትቲዩት የፖሊሲ ጉዳዮች ተመራማሪው ዶክተር ግርማ ተሾመ እንደሚሉት፤ ግብጽ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ እንዳትጠቀም ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች። በቅርቡ በዓለም ባንክና በአሜሪካ አደራዳሪነት የተካሄደው ድርድርም የዚሁ የግብጽ ሴራ አካል ነው። የዓለም ባንክና አሜሪካ በታዛቢነት ገብተው በመጨረሻ ላይ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ፊርማ ለማስፈረም መሞከራቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ በመጨረሻ ላይ የዓለም ባንክና የአሜሪካ አደራዳሪነትን አልቀበልም፣ ሉዓላዊነቴን አስከብራለሁ ብላ ጠንካራ አቋም በመያዟ ግብጽ አስባ የነበረው ነገር አልተሳካም። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚያ በኋላም አቋሙን በግልጽ በማሳወቁ ግብጾች የሄዱበት መንገድ እንደማያዋጣቸው ተረድተዋል።
ግብጾች ወደ ድርድሩ ለመመለስ የፈለጉበት በሁለት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ በአንድ በኩል እውነተኛ ድርድር በማካሄድ ከስምምነት ለመድረስ በማሰብ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን በዚህ ክረምት ጀምራለሁ ማለቷ ከምሯ እንደሆነ በመገንዘባቸውና ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ የያዘችውን ጠንካራ አቋም በመገንዘባቸው የውሃ ሙሌት ድርድር ሳይካሄድ እንዲጀመር ስለማይፈልጉ ወደ ድርድርና ውይይት መድረኩ ተመልሰው ለመደራደርና ከስምምነት ለመድረስ በማሰብ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
ግብጾች ወደ ድርድሩ እንመለሳለን ያሉት እውነተኛ ድርድር አካሂደው ወደ ስምምነት ለመድረስ ነው የሚለው እጅግ አጠራጣሪ እንደሆነም ይናገራሉ ። እንደ ዶክተር ግርማ ማብራሪያ ሁለተኛው ቢሆን ግብጽ ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ እንደነበረው ድርድር እስኪያልቅ በሚል ስበብ በቅርብ ርቀት ሆነው የግድቡን ግንባታና የውሃ ሙሌት ጊዜ ለማራዘም ሊሆን ይችላል። ግብጾች የግድቡን ግንባታ ለማዘግየት የተለያዩ ዘዴዎችን ሲጠቀሙ ኖረዋል። ድርድሮች በግብጾች ነው ሲደናቀፍ የነበረው። ከዚህ ቀደም የተደረጉ ድርድሮች ለግብጾች ጊዜ መግዣ ሆነዋል። ስለግድቡ መረጃ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ኢትዮጵያ ለሰላም እና ለአብሮነት ካላት ጽኑ ፋላጎት የተነሳ በተደረጉ ድርድሮች ከሚጠበቅባት በላይ መንገድ ሄዳ ለግብጾች ማድረግ ከሚገባት በላይ አድርጋለች የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ አሁንም ግብጾች በተመሳሳይ ድርድር በሚል የሆነ ጥቅም እናገኛለን የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።