ግንቦት ሃያን ያመጡ ታጋዮች ዓላማ ኢትዮጵያን ወደ ግንቦት ሃያ ሁለት መውሰድ እንጂ ወደ ግንቦት አሥራ ዘጠኝ መመለስ አልነበረም — ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የግንቦት ሃያ ድል መታሰቢያ በዓልን አስመልክተው ተከታዩን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል
እንኳን ለግንቦት ሃያ የድል መታሰቢያ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ።
Imageግንቦት ሃያ የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ከቀየሩ ዕለታት መካከል አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ለማድረግ አያሌ ታጋዮች እጅግ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ነፍስ ሠውተዋል፡፡ የግንቦት ሃያ ታጋዮች የነፍስ ዋጋ የከፈሉለት ዓላማ ግፍና ጭቆና፣ አድሎና ወገንተኝነት ቆሞ፤ እኩልነት ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ነው፡፡
ግንቦት ሃያን ማክበር ያለብን እነዚህን ዓላማዎች እያሰብን መሆን አለበት፡፡ ቀኑን የምናስበው በግንቦት ሃያ ላይ ተቸክለን ሳይሆን ወደፊት እየሄድን የኋላውን እየገመገምን መሆን አለበት፡፡ ግንቦት ሃያን ያመጡ ታጋዮች ዓላማ ኢትዮጵያን ወደ ግንቦት ሃያ ሁለት መውሰድ እንጂ ወደ ግንቦት አሥራ ዘጠኝ መመለስ አልነበረም፡፡ ሀገራቸው በሁሉም መመዘኛ ግንቦት ሃያን አልፋ፣ ግንቦት ሃያ አንድንም ተሻግራ፣ ወደ ግንቦት 22 መድረስ ነበር፡፡
የግንቦት ሃያ ታጋዮችን ዓላማ የምናሳካው በሁለመናዋ ከግንቦት 19 የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ከቻልን ብቻ ነው፡፡ የብልጽግና ጎዳናችን ዓላማ ግንቦት ሃያ ላይ ቆሞ ግንቦት አሥራ ዘጠኝን እያሰቡ መኩራራት ሳይሆን ሀገራችን ወደ ግንቦት 22 ማስፈንጠር ነው፡፡ ይህ ማለትም ሀገራችን ከነበረችበት አስከፊ ሁኔታ ማላቀቅ ብቻ ሳይሆን መድረስ ወደነበረባት የላቀ ደረጃ ማድረስ ነው፡፡ የግንቦት ሃያ የድል መታሰቢያ በዓልን ሰናከብር በተባበረ ክንድ ከግንቦት ሃያ የሚልቅ፣ ወደ ግንቦት 19 እንዳንመለስ የሚያደረግ ምጡቅ ሥርዓት ለመገንባት ቃላችን የምናድስበት እና ወደ ላቅ ውጤት ለመቀየር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የምንገባበት መሆን ይገባዋል፡፡
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ በአጥንትና ደማቸው ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ላቆዩ ሰማዕታት!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ግንቦት 19/2012 ዓ.ም