በሱዳን ድንበር አካባቢ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመቆጣጠር አሳሳቢ በመሆኑ የፌዴራል መንግስትን ድጋፍ ጠይቋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል የአማራ ክልላዊ መንግሥት አሳሰበበ በአማራ ክልል ከሱዳን ድንበር የሚዋሰነው የምዕራብ ጎንደር ዞን በጠረፋማ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እያደረገ ያለው ጥረት ከአቅሙ በላይ መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል። የአማራ ክልል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ሃይል ወረርሽኙን ለመከላከል እየተሰሩ ባሉና ቀጣይ ትኩረት ሊሰጥባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዛሬ ማምሻውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር)፣ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ደረጃ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የግብረ ሀይሉ ሰብሳቢ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) እና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገረመው ገብረጻድቅ ናቸው በጋራ መግለጫ የሰጡት።
ዶክተር ሙሉነሽ እንደተናገሩት ግብረ ሀይሉ የኮሮና ቫይረስ ሁለንተናዊ ቀውስ እንዳያስከትል ጥረት እያደረገ የሚገኝ ቢሆንም በሚጠበቀው ልክ አበረታች ውጤቶች እየታዩ አይደሉም። በተለይ በምዕራብ ጎንደር ዞን ጠረፋማ ቦታዎች እየተስተዋለ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ አስረድተዋል። እስካሁን በነበረው ሂደት የክልሉ መንግስት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የማቆያ ቦታዎችን ለማስፋትም ሆነ አስፈላጊ ግብአቶችን ለማሟላት ሲሰራ የቆዬ መሆኑንም ዶክተር ሙሉነሽ ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ግን ችግሩ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል። በየቀኑ የሚገቡ ግለሰቦችን ታሳቢ ያደረጉ የማቆያ ቦታዎች፣ የመመርመሪያና የህክምና መስጫ ማዕከል በአቅራቢያው አለመኖር በቅድመ መከላከሉ ሥራ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ እንደሆነም አስረድተዋል።
በአካባቢው የምርመራ ማዕከል ባለመኖሩ ወደ ጎንደር ከተማ የደም ናሙናው እንዲላክ መደረጉም በአሠራሩ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑ ተገልጿል። እንደ መግለጫው ዞኑ 19 የመግቢያ በሮች ያሉት በመሆኑ የመከላከል ሥራውን ፈታኝ አድርጎታል። በየጫካው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ሰዎች እንዳሉም ተጠቁሟል። በየቀኑ ከ4 መቶ በላይ ሰዎች እንደሚገቡም ተነስቷል። አብዛኛዎቹ ከሱዳን ሀገር በተለያዩ የጉልበት ሥራዎች ተሰማርተው የቆዩ ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የሄዱ ናቸው።
በአካባቢው ራሱን የቻለ የአደጋ ምላሽ ማዕከል፣ የህክምናና የምርመራ ማዕከላት መቋቋም እንዳለባቸው በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ አብዛኛዎቹ ለይቶ ማቆያዎች ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው ተጨማሪ ስድስት ማቆያዎች በፍጥነት እንዲሠሩ መወሰኑንም ዶክተር ሙሉነሽ አንስተዋል። በመሆኑም የፌዴራል መንግስቱ ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ግባቸውን እንዲመቱ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፤ በቀጣናው ያንዣበበው ስጋት በሀገሪቱ ህልውና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም መግለጫውን የሰጡት የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች አሳስበዋል።
ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ካሉ ኢትዮጵያውያን ውጭ የሌሎች ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውም በመግለጫው ተነስቷል፤ የፌዴራል መንግስቱ በመጠለያ፣ በጤናና መሰል ጉዳዮች ትኩረት ከማድረግ ጎን ለጎን ለፀጥታና ሀገራዊ ደኅንነት ጉዳይም አፅንኦት መስጠት እንደሚገባው ነው የተጠየቀው።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) በበኩላቸው በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የማኅበረሰቡ ተነሳሽነት እየተቀዛቀዘ መምጣቱን አንስተዋል። እንደ ሰርግና ሀዘን ያሉ ማኅበራዊ ኩነቶች እየተከወኑ እንደሆኑም ጠቅሰዋል። አለመጠንቀቅ አስከፊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል ስለሚችል እያንዳንዱ ሰው ቅድመ መከላከሉ ላይ ትኩረት ማደረግ እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምንጭ፦ አብመድ