ሮባት ሶፊያ አዲስ አበባ ገብታለች፣ አንዳንድ አካላቷ ግን አውሮፕላን ጣቢያ ጠፍተዋል

በጀርመን በርሊን ኤክስፖ ቆይታ ያደረገችው ሮቦት ሶፊያ ዛሬ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ብትደርስም በፍራንክፈርት የአውሮፕላን ማረፊያ የተወሰነ ክፍሏን የያዘው ሻንጣ መጥፋቱ ታውቋል።

ይህም በእርሷ ላይ የተወሰነ ጉድለት የሚፈጥር ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አይኮግ ላብስ የቴክኖሎጂ ካምፓኒ ባለሙያዎች ለማስተካከልና የጠፋውን ለመተካት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ እንደሆነ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደኅንነትና ግርግርን ለማስወገድ በሚል ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ያደረጉላት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ብቻ ነበሩም ተብሏል። ቀደም ባለው መርሀ ግብር በአቀባበሉ ላይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንደሚገተኙ ተነግሮ ነበር።

ዛሬ ቀትር ላይ ‘ከድንቅነሽ እስከ ሶፊያ’ በሚል ርዕስ በብሔራዊ ሙዚየም የሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት እየሄዱ እንደሆነ ሚኒስትሩ ከደቂቃዎች በፊት ለቢቢሲ በስልክ ተናግረዋል።

የአይኮግ ላብስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት አሰፋ በበኩላቸው ሻንጣው በጀርመን ፍራንክፈርት የአውሮፕላን ማረፊያ እንዸጠፋ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎቹ የጎደለውን ለመሙላት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

VIDEO