~”እስር ቤት ውስጥ የተደራጀ ቡድን አለ፣ እስር ቤት ውስጥ ያለው አይ ኤስ ነው”

~”ውጭ ያለው ሕዝብ እንደመር እያለ እኛን እየቀነሱን ነው”

~”ከቂሊንጦ እስር ቤት ካላስወጣችሁን በሚቀጥለው የሚመጣው አስከሬናችን ነው”
ተከሳሾች

በቂሊንጦ ቃጠሎ በእነ አርጋው ሞገስ ክሰ መዝገብ የተከሰሱት አርጋው ሞገስና ቴዎድሮስ ዳንኤል ፍርድ ቤት ቀርበው እውነታውን በመናገራቸው ብቻ በቂሊንጦ እስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ለፍርድ ቤት አመልክተዋል። ተከሳሾቹ ዛሬ ሰኔ 22/2010 ዓም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3 ወንጀል ችሎት ቀርበው በድብደባ የተጎዳውን አካላቸውን አሳይተዋል።
1ኛ ተከሳሽ አርጋው ሞገስ ግራ እጁ በፋሻ ተጠቅልሎ ከአንገቱ ጋር ታስሮ የመጣ ሲሆን አራት የእጅ ጣቶቹ መሰበራቸውን ለፍርድ ቤት ተናግሯል። እንዲሁም እግሩ በሚስማር መመታቱን አሳይቷል። አራቱ የእጅ ጣቶቹ መጎዳታቸውን የሚያሳይ የህክምና ውጤት (የራጅ ውጤትም) ለፍርድ ቤቱ አሳይቷል
በተመሳሳይ የቀኝ እጁ በፋሻ የታሸገው ቴዎድሮስ ዳንኤልም ፍርድ ቤት መጥቶ በሚናገረው እስር ቤት ውስጥ ድብደባ እንደተፈፀመበት ገልፆአል። ልብሱን አውልቆ በድብደባ የበለዘ ሰውነቱን ለፍርድ ቤቱ አሳይቷል።

ተከሳሾቹ እስር ቤት ውስጥ አብራራው በሚባል ግለሰብ ትዕዛዝ መደብደባቸው ገልፀዋል። ድብደባ የተፈፀመባቸው ጭንብል ባጠለቁ ሰዎች እንደሆነ በመግለፅ “የተደራጀ የማፍያ ቡድን አለ” ሲሉም ገልፀዋል።

ተከሳሾቹ “እስር ቤት ውስጥ የተደራጀ ቡድን አለ፣ እስር ቤት ውስጥ ያለው አይ ኤስ ነው፣ውጭ ያለው ሕዝብ እንደመር እያለ እኛን እየቀነሱን ነው፣ ከቂሊንጦ እስር ቤት ካላስወጣችሁን በሚቀጥለው የሚመጣው አስከሬናችን ነው፣ ከፈለጋችሁ ወደ ሌላ እስር ቤት ላኩን” ሲሉ በቂሊንጦ እስር ቤት በሚፈፀምበቸው ድብደባ ለሕይወታቸው እንደሚሰጉ አመልክተዋል።