ልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በተደረገ ድንገተኛ ምርመራ 40 የህግ ታራሚዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተገኘባቸው 365 ሰዎች ውስጥ 228 የሚሆኑት በአዲስ አበባ እንደሚገኙ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የልደታ ክ/ከተማ 40 በመቶ የሚሆነውን ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች ቁጥር ሲይዝ አዲስ ከተማ ክፍለከተማ በሁለተኛነት ድርሻውን መያዙን ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል፡፡
ይህም ቫይረሱ በአዲስ አበባ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክት እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እንዲሁም ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 16 በመቶ መድረሱንም ዶ/ር ሊያ አስታውቀዋል፡፡
የቫይሱን ስርጭት ለመቆጣጠርም ከቫይረሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ቅኝት የማድረግ ስራ ዋነኛ ተግባር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ ናቸው፡፡
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተደረገ ቅኝት ከቫይረሱ ጋር ንክኪ ከነበረው አንድ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው 32 ግለሰቦች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ በወረዳው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በተደረገ ድንገተኛ ምርመራ 40 የህግ ታራሚዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እስካሁን 62 ሺህ 300 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ካለፉት 2 ወራት ይበልጥ በ2ሳምንት ውስጥ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 63 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡