የምህረት አሰጣጥ እና አፈጻጸም ስነ ስርዓት አዋጅ ፀደቀ

የምህረት አሰጣጥ እና አፈጻጸም ስነ ስርዓት አዋጅ ፀደቀ

የምህረት አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ስርዓት አዋጅ 1089/2010 ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ከአደመጠ በኋላ አዋጁን አፅድቋል።
በዚሁ መሰረት አዋጁ በአብላጫ ድምጽ በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ እንዲጸድቅ ተደርጓል።አዋጁም በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ የጸና እንደሚሆን ነው የተገለጸው።

አዋጁ የፖለቲካ ጥፋቶችን፣ አገር መክዳት፣ የአመጽ ወንጀለኞችንና በአገርና በመንግስት ላይ የመነሳሳት ወንጀል ለፈጸሙና በህግ በሚሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው ለመመለስና ህግና ስርዓትን ለማክበር ለተዘጋጁ ሰዎች ምህረት የሚደረግበትን ስነ ስርዓት የሚደነግግ ነው።

በማንኛውም የወንጀል አይነቶች ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾች ወይም ፍርደኞች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ቢገልጽም፤ የሰው ዘር በማጥፋት፤ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ በመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር እና ኢ-ሰብአዊ የድብደባ ድርጊት መፈጸም ወንጀሎች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ያስቀምጣል።

የወንጀል ድርጊቱ በአገር ሉአላዊነት ላይ የሚያስከትለው ወይም ያስከተለው ተጽእኖ ምህረት ለመስጠት ከግምት ውስጥ ከሚገቡ ሁኔታዎች ውስጥ ተጠቅሷል።

ምንጭ ኢዜአ