በፌደሬሽን ምክር ቤት ማህተም ወልቃይት ላይ ያረፈው የትህነግ/ህወሓት ውሳኔ (ጌታቸው ሺፈራው)

በፌደሬሽን ምክር ቤት ማህተም ወልቃይት ላይ ያረፈው የትህነግ/ህወሓት ውሳኔ (ጌታቸው ሺፈራው)

ትህነግ/ህወሓት እንደወልቃይት ጉዳይ የራስ ምታት የሆነበት ጉዳይ ያለ አይመስልም። ላለፉት 27 አመታት በርካታ የመብት ጠያቂዎች አፍኗል፣ ገድሏል፣ ብዙ ፕሮፖጋንዳ ሰርቷል። ይህም ሆኖ የወልቃይት ጉዳይ እየበረታ መጣ እንጅ አልቀዘቀዘም። ከትህነግ/ህወሓት ጋር አብረው የታገሉት እነ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የጥያቄው ፊት አውራሪ እስከመሆን ደረሱ። የሚደረገው አፈና እና ግድያ የወልቃይትን ጥያቄ ከማፈን ይልቅ አደባባይ አወጣው። በተለይ ከ2007 ዓም ታህሳስ ወር ጀምሮ ጥያቄው በተደራጀ መንገድ መቅረብ ጀመረ። ሆኖም በሕጋዊ መንገድ ጥያቄ ያቀረቡት መታደን ጀመሩ። ሕገ ወጥ ጦር ዘመተባቸው። በቅርቡ የትህነግ/ህወሓት አመራሮች በግልፅ የወልቃይትን ጥያቄ ለማድበስበስ ሞክረዋል። እነ ደብረፅዮን “የወልቃይት ሕዝብ የጎንደር ከተማ ሕዝብ ስማችን አያንሳ ብሏል” ብሎ የጭንቀቱን ተናግሯል። በተለያዩ የትህነግ መግለጫዎች ለትግራይ ሕዝብ አደጋ ብለው የሚገልፁት በወልቃይት ላይ የሚነሳውን ጥያቄ ነው። በወልቃይት ጉዳይ ትህነግ/ህወሓት ይፋዊ ጦርነት አውጇል። የወልቃይት ሚሊሻዎችን “ጦርነት ብንገጥም ከማን ጋር ትሆናላችሁ?” ብሎ ጠይቋል። የፋሲል ከነማ ማሊያ፣ የአጤ ቴዎድሮስ ፎቶ ሕገወጥ ተደርጓል። ይህ የህወሓት አቋማ ሆኗል!
የትህነግ/ህወሓት ስራ አስፈፃሚ በምሬት መግለጫ ሲያወጣ ቀዳሚው ጉዳይ ወልቃይት ነው። በቅርብ በወጣው የስራ አስፈፃሚው መግለጫ “ጠላቶቻችን እንከላከለለን” ይላል። ይህን መግለጫ ካወጡት የስራ አስፈፃሚ አባላት መካከል አንዷ ኬርያ ኢብራሂም ነች። ኬርያ በቅርቡ የብአዴኑን ያለው አባተ ተክታ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆና ተቀምጣለች። ወይዘሮ ኬርያ በዚህ ተቋም ስትቀመጥ ወልቃይትን ታሳቢ ተደርጎ ነው። ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ ከትግራይ ክልል ውጭ ያለውን ሕዝብ የማንነት ጥያቄ እያስነሱ ለማበጣበጥ ለትህነግ ቁልፍ ሚና መጫወት ትችላለች።

የወልቃይት ማንነት ጠያቂዎች ከ2007 ዓም ጀምሮ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት ጥያቄ በመታፈናቸው ምክንያት ተቋርጦ፣ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በአዲስ መልክ ስራ ጀምረዋል። በቅርቡ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆነችው የትህነግ ስራ አስፈፃሚ አባል የትህነግን አቋም በፌደሬሽን ምክር ቤት ማህተም ወልቃይት ላይ ውሳኔ አስተላልፋለች።

የትህነግ ስራ አስፈፃሚና የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በሆነችው ኬርያ በኩል በቁጥር-ፌደም/ኢ6/5/288 በቀን-04/10/2010 የፃፈውን ደብዳቤ የወልቃይን ጥያቄ ውድቀወ ለማስረግ 3 ምክንያቶች ጠቅሷል! አንደኛውን ዋነኛው ከትህነግ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

የመጀመርያው እና በቀጥታ ከትህነግ ጋር የተያያዘው የወልቃይትን ጥያቄ ለመመለስ የተሰጠው ምክንያት “በክልሉ በሚገኙት የተለያዩ የመስተዳድር እርከኖች ቀርቦ አጥጋቢ መፍትሔ ያልተሰጠው ስለመሆኑ ከቀረበው ማመልከቻ ማረጋገጥ ባለመቻሉ” የሚል ነው። ትህነግ ጥያቄው ቀርቦለት መፍትሄ ስላለመስጠቱ መረጃ የለም ብላ የፃፈችው፣ ለመብት ጠያቂዎቹ ብቻ ሳይሆን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ መልስ አልሰጥም ያለው የትህነግ ስራ አስፈፃሚ አባል ነች። ሕጋዊ እርምጃ ባይሰጥም፣ ለህጋዊ ጥያቄ ትህነግ ህገወጥ እርምጃ መውሰዱን ታውቃለች! የህጋዊም ባይሆን ለሕገ ወጡ ስራ አስፈፃሚ አባል ነችና!

የወልቃይት እውነታ!
……………………
የወልቃይት ማንነት ጠያቂዎች ታህሳስ በ2007 ዓም ከመቶ ሽህ በላይ ፊርማ በማሰባሰብ ለፌደሬሽንን ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበዋል። ይህ ፊርማ ለትግራይ ክልል፣ ለአማራ ክልልም ገብቷል። በተመሳሳይ 2008 ዓም ህዳር ወር ለፌደሬሽን ምክር ቤት ካስገቡ በኋላ ታህሳስ 7/2008 ዓም ለትግራይ ክልል አስገብተዋል። ወይዘሮ ኬርያ በመጀመርያ መስፈርትነት ያቀረበችው በየደረጃው ባለ አስተዳደር አልቀረበም የሚል ነው። ሆኖም ታህሳስ 2008 ዓም ጥያቄያቸውን መቀሌ ሲያቀርቡ የጠበቃቸው ወከባ ነው። ከመቀሌ መልስ ወደ ሁመራ (ዞን) በማቅናት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። በዚህ ወቅት አፈና ደርሶባቸዋል።
የትግራይ ባለስልጣናት ውክልና የላችሁም በማለታቸው በመላ ወልቃይት ወኪሎች ተመርጠው ከአማራ ክልል ጀምሮ ወደ ፌደራል መንግስቱ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚህም መሰረት ጥር 2008 ዓም ወደ ባህርዳር ከዛም ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል። ሆኖም ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እንጦጦ ላይ ትግርኛ ተናጋሪዎች በመሩት ፌደራል ፖሊስ ታግተው እንዲመለሱ ተደርገዋል። በአንድ ላይ ተሰባስበው ከመሄድ ተነጣጥለው ወደ አዲስ አበባ መግባት እንዳለባቸው ወስነው እንደገና ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ጥር 25/2008 ዓም ለፌደሬሽን ምክር ቤት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ከፌደሬሽን ምክር ቤት ሲወጡ በር ላይ በትህነግ/ህወሓት ባለስልጣናት ትዕዛዝ ታፍነው እነ ተክላይ መብርሃቱ ወደሚመሩት ማዕከላዊ ታስረዋል። በእነ ተክላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ደርሶባቸው ምሽት 4 ሰዓት ሲፈቱ በነጋታው ጥር 26 የደረሰባቸውን አፈና ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ አስረድተው ተመልሰዋል።

መጋቢት 26/2008 ዓም ፌደሬሽን ምክርቤት ለትግራይ ክልል ህገ መንግስቱ በሚያዘው መሰረት መልስ እንዲሰጥ ደብዳቤ ይፅፋል። ሆኖም የትግራይ ክልል አስተዳደር ፌደሬሽን ምክር ቤት ለፃፈለት ደብዳቤ እንኳ መልስ መስጠት ፈቃደኛ አልነበረም። የትግራይ ክልል መንግስት ለፌደሬሽን ምክር ቤት ትዕዛዝም መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የወልቃይት ኮሚቴ ጉዳዩን ለህዝብ አሳውቋል። ኬርያ ኢብራሂም “በየ እርከኑ ቀርቦ አጥጋቢ መልስ እንዳልተሰጠበት አላስረዳችሁም” ያለችለት የትግራይ ክልል መልስ ባለመስጠቱ ሕዝብን ማወያየትን ምርጫቸው አድርገው ቆይተዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ለፃፈው ሕጋዊ መልስ ያልሰጠው የትግራይ ክልል ሕገወጥ እርምጃዎችን ግን ወስዷል። ለአብነት ያህልም ሀምሌ 5/2008 ዓም በርካቶቹን የወልቃይት ሕዝብ የወከላቸውን አስሯል። በኮል ደመቀ ዘውዱ ላይ ጦር አዝምቷል። አብዛኛዎችን በሽብር ክስ ቀርቦባቸዋል፣ ተገድለዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ታፍነው ጠፍተዋል። ይህ የሆነው ኬርያ ኢብራሂም አባል በሆነችበት የትህነግ/ህወሓት ስራ አስፈፃሚ ትዕዛዝና የበላይነት ነው።
ትህነግ /ህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል አስተዳደር ለወልቃይት ጥያቄ ሕጋዊ መልስ ስጥ ተብሎ ከፌደሬሽን ምክር ቤት ሲፃፍለት፣ ለዚህ ተቋም አልታዘዘም። መብት ጠያቂዎቹ ላቀረቡት ሕጋዊ መልስ የገጠማቸው እስር፣ ግድያ ስደት ነው። በኮል ደመቀ ላይ ከዘመተው ጦር ባሻገር የሌላ ሰው የተዘጋ መዝገብ ተከፍቶበታል። ከዚህ ሁሉ ህገ ወጥ እርምጃ ኬርያ ኢብራሂም አባል የሆነችበት ትህነግ/ህወሓት ዋነኛ ተዋናኝ ነው። ትህነግ ፌደሬሽን ምክር ቤት ለሰጠው ደብዳቤ መልስ አልሰጠም። ከሶስት ወር በፊት ደግሞ ለፌደሬሽን ምክር ቤት መልስ ለመስጠት አሻፈረኝ የሚለው ትህነግ ስራ አስፈፃሚ አባል መልስ የተነፈገው ተቋም ኃላፊ ሆናለች። በዚህ ኃላፊነትም የወልቃይትን ጥያቄ እንደ ተቋም ሳይሆን እንደ ትህነግ/ህወሓት ስራ አስፈፃሚ መልስ ሰጥታበታለች። አቶ ያለው አባተ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በነበረበት ወቅት በትህነግበ/ህወሓት ዘንድ “ለወልቃይት ማንነት ጠያቂዎች አዝማሚያ አሳይቷል” ተብሎ ተወቅሷል። የትህነግ ስራ አስፈፃሚ አባል የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አባል ከሆነች በኋላ የወልቃይት ማንነት ጠያቂዎች ጉዳዩን ሲያቀርቡ የህግ ክፍሉ “አፈ ጉባኤዋ አዲስ ስለሆኑ ጉዳዩን እናስረዳቸዋለን” ብሎ የነበር ቢሆንም ወይዘሮ ኬርያ ከሕግ ክፍሉ ሳይሆን የትህነግ ስራ አስፈፃሚ አቋም መሰረት መልስ መስጠቷ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በመልሱ ላይ በሰጠው ማብራሪያ ገልፆአል።

ህግ ቢኖር በሰላማዊ መንገድ ሕጋዊ የመብት ጥያቄ ያነሱት የሕዝብ ወኪሎች ላይ አፈና የወሰደው አካል ይጠየቅ ነበር። ሕግ ቢኖር በሕጋዊ መንገድ የተጠየቀው የማንነት ጥያቄ ሕጋዊ መልስ ይሰጠው ነበር። ሕግ ቢኖር የፌደሬሽን ምክር ቤት ለጠያቂዎቹ መልስ ስጥ ብሎት መልስ ያልሰጠው የትግራይ አስተዳደር ይጠየቅ ነበር። ሕግ ቢኖር ማንነት ጠያቂዎችን በማፈን፣ በማሰርና በመግደል ላይ የሚገኘው የትህነግ/ህወሓት ስራ አስፈፃሚ አባል የፌደሬሽን ምክር ቤት ማህተምን ተጠቅማ በትህነግ/ህወሓት አቋም ላይ ማህተም እንድታሳርፍ አይፈቀደም ነበር። ዛሬ የትህነግ/ህወሓት አቋም ላይ የፌደሬሽኑን ማህተም አሳርፋ የወልቃይት ጥያቄ “ውድቅ ነው” ያለች የትህነግ ስራ አስፈፃሚ በሌላው ክልል ለሚያበጣብጡት ሕዝብም ቀጣይ አጀንዳቸው ላይ ማህተም እያሳረፈች ማንነት ብትሸልም የሚጠይቃት ያለ አይመስልም። የተቀመጠችው ለዚሁ የትህነግ/ህወሓት አጀንዳ ነውና!