(ኢዜአ) ”ከሁሉም በፊት የህዝብ ሰላም፣ ደህንነትና ጤና ካልተጠበቀ ፖለቲካም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት አይኖርም” ሲሉ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው በመስራት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
አቶ ተስፋዬ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወቅታዊ የትኩረት አቅጣጫ መካከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አንዱ ነው።
የፓርቲው የምንጊዜም ትኩረት የሕዝብ ሰላም፣ ደህንነትና ጤና እንደሆነም ገልጸዋል።
ሁሉም ተግባር ማዕከሉ ሕዝብ በመሆኑ ፓርቲው ለህዝብ ጉዳዮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
”የሕዝብ ሰላም፣ ደህንነትና ጤና ካልተጠበቀ ፖለቲካም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲና ምርጫ አይኖርም” ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ።
ፓርቲው ምርጫም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ከሕዝብ ጤንነት መረጋገጥ በኋላ ይደርሳሉ በሚል የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
”የህዝብን ደህንነት ከማስጠበቅ ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ለሀገር የማይጠቅሙና የፖለቲካ ቁማሮች ናቸው” ብለዋል።
ከዚህ ውጪ ጥያቄ የሚያቀርቡ አካላት ጥያቄያቸው በህገ-መንግስቱ የሚመለስ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።
ምርጫው በቦርዱ በተያዘለት የጊዜ መረሐ ግብር እንዲካሄድ መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት ያደርግ በነበረበት ወቅት ምርጫው መካሄድ እንደሌለበት ሲሞግቱ የነበሩ አካላት አሁን በወረርሽኙ ምክንያት እንዲራዘም መደረጉን መቃወማቸው ተቀባይነት እንደሌለውም ገልጸዋል።
ምርጫው ተጨማሪ የውዝግብ ምንጭ እንዲሆን የሚፈልጉ አካላት በየጊዜው እርስ በርሱ የሚጣረስ አቋም እየያዙ እንደሆነም አመልክተዋል።
በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ቀን ተቆርጦለት የነበረው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል ቦርዱ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫው እንዲራዘም መወሰኑ ይታወሳል።