በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ወንዶች የወሲብ ጥቃት ይደርስባቸዋል ፤ ይደፈራሉ ።

በእስረኞች ላይ የተፈፀመውን በደል ባሰብኩ ጊዜ አሁንም ያመኛል። በአንድ ወቅት ወንዶች የሚታሰሩበት ቂሊንጦ እስር ቤት እስረኞችን ለመጠየቅ ሄጄ አንደኛው እስረኛ ፖሊስ እንዳያየው ተጠንቅቆ የተጠቀለለች ብጣሽ ወረቀት ሰጠኝ፣ እንድደብቃት ነገረኝ። ስለ አንድ ጭካኔ አወራኝ። በዚህ ሀገር ያልተፈፀመ ነገር የለም። ግን ይህኛውን ለመስማት እንኳን ይዘገንናል።

ያችን ወረቀት እንደምንም ብየ ከእስር ቤት አስወጣኋት። የአራት ግለሰቦች ስም ሰፍሮባታል። ትንሽ መግለጫም ጨምሮባታል። አይጣል ነው!

በሌላ ጊዜ በጣም የማምነው ሰው ሌላ ብጫቂ ወረቀት ከእስር ቤት ላከልኝ። ከፍቼ ሳየው የእነዛ አራት ወጣቶች ስም ሰፍሮበታል። ወጣቶቹ ማዕከላዊ በነበሩበት ወቅት የተደፈሩ ናቸው። ስማቸውን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መዘርገፍ ቢከብደኝ Muluken Tesfawን አነጋገርኩት። ሚዲያ ላይ ባይለቀቅ ይሻላል ብለን ተስማማን። ብዙውን ጊዜ ስንዘግብ ከበደሉ መብዛት የተነሳ የምናጋንን የሚመስለውም አይጠፋም። ለሕዝብ ሞራል ስንል የተውነውን ደግሞ የሚያውቅ ጥቂት ሰው ነው!

የእስረኞቹን ጉዳይ በምንዘግብበት ወቅት ትልቁ ፈተናችን ከገዥዎቹ ይመጣል የሚባል ዱላ አልነበረም። እሱን ቆርጠን ገብተንበታል። አሳዛኝ የነበረው (በተለይ መጀመርያ አካባቢ) አለመታመኑ ነው። የምናውቀው ሰው ሁሉ “ግን እውነት እንዲህ ይደረጋል?” ብሎ ይጠይቀናል። የሰው ልጅ ላይ ይህ አይፈፀምም ብሎ በቅንነት በማመን ወንድሞቹና እህቶቹ ላይ የተፈፀመውን የሚጠራጠረው ብዙ ነበር። ለእኔ ይህ ትልቁ ህመም ነበር።

አሁን ኢቲቪ ጥቂቶች እየጮሁ ግን ጩኸቱ፣ የቁራ ጩኸት ሆኖ የነበረውን የእስረኞቹን ሰቆቃ በጣም በጥቂቱ እየዘገበ ነው። ነገ ደግሞ ፍትህ ያገኙ ይሆናል! ሁላችን ከህመማችን የምንፈወሰው ያኔ ነው!