ጎርጎርዮስ የደረሰው “መጽሐፈ ቅዳሴ”

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

ማሰሰቢያ፦   ይህች ጦማር ጎርጎርዮስ በደረሰው መጽሐፈ ቅዳሴ ላይ የተመሰረተች  ናት። ጎርጎርዮስ የደረሰው መጽሐፈ ቅዳሴ  በ 18 ገጾች ተወስኖ፤  በ 107 ቁጥሮች ተከፍሎ በትንሣዔ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤት በ 1994 ዓ/ ምህረት አዲስ አበባ በታተመው ከ14ቱ ውስጥ አንዱ ነው ። የጎርጎርዮስ ድርሰት ከገጽ 269 እስከ 286 ገጽ ላይ ኛል። የመጽሐፉ ይዘት በዚህ ዓመት የገጠመንን ካሮና ቫይረስ የመሰለ ክስተት ጎርጎርዮስን የገጠመው ይመስላል።

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ራቁቷን የቆመች ቀን ሳምንት ወርና ዓመት የሉም የተደራረቡ ክስተቶችን በዓላት የተሸከሙ ናቸው ። በውስጥ ከሀዲወች በውጭ ወራሪወች የሚያስጠላትና የሚያስተቻትም  የድርብርብ ትዝታ ማህደርና መዘክርነቷ ነው። ሰው በማወቅም ባለማወቅም የሚያመጣቸው የመከራና የደስታ ክስተቶች በዕለታት በሳምንታት በወራትና በዓመት እየታዘሉ  የሚከሰቱ ናቸው። በተረት፤ በአፈ ታሪክ፤  በቅኔ በግድላትና በታምራት መጻሕፍት በብራና ይመዘገባሉ፤ በስም አጠራራቸው አማካይነት በዚያው ዘመን ተጸንሰው በሚወለዱ  ሕጻናት ሕሊና ላይም ይቀርጿቸዋል ። ከነሱ የተረከብናቸውን ክስተቶች የኛንም ደርበን በሚቀጥለው ትውልድ  ሕሊና ላይ እንድንቀርጻቸው በምሳሌነት አስተምረውናል። የዚህ ዓመት ሆሳዕና ደርባ ለያዘቻቸው ክስተቶች ሁሉ መታሰቢያ ትሆን ዘንድ እኔም የጎርጎርዮስ ቅዳሴ ያለንበትን ዘመን ሲቃኘው በሚል ርእስ በዘመኔ ላላችሁት ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቼ በዘንድሮው ሆሳዕና በዐል ላይ ተደርበው የተከሰቱትን አቀረብኩላችሁ።

================================*********============================

ጎርጎርዮስ  በዚህ ዓለም ስንት ዘመን እንደኖረና በዘመኑ ዑደት ውስጥ ሆሳዕናን ስንት ጊዜ   እንዳከበረው አላውቅም። የጎርጎርዮስን እዚህ ላይ ላቁመውና፤ ካይሮቫይረሷ ተከስታ ፊቴን በደቂቃ ስንት ጊዜ እንደምነከው ሲነገር እስክሰማ ድረስ እንደማላውቅ፤ እስካሁን በቆየሁበት ዘመኔ ሆሳዕናን ስንት ጊዜ እንዳከበርኩ እኔም አላውቅም።  በወጣትነት በማእከላዊው ወይም በእርግና ዘመኑ ይሁን በየትኛው ዘመኑ ጎርጎርዮስ  ብዙ ክስተቶችን ያካተተውን በድርሰት እንደደረሰው አላውቅም። ግን  ጎርጎርዮስ  ይህን መጽሐፍ በደረሰበት አመት  ተመሳሳይ ክስተቶች ተደራርበው ገጥመውት እንደነበረ ከድርሰቱ ይዘት እረዳለሁ።

ጎርጎርዮስ የአምላክን ምጡቅ ረቂቅና ኃያልነት ለመግለጽ  ”ሥውር ውእቱ እምህሊና ኩሎሙ መላእክት አልቦ ዘየአምሮ መላእክት ወአልቦ ዘየአምር ለህላዌሁ ወአልቦ ዘይሄልቆ ዘለሀኮ በእዴሁ( 11)የመሳሰሉትን  ሐረጎችን እንደ አዝማች በመጠቀም በዘመኑ በዋለው ሆሳዕና ላይ ተደርቦ የገጠመውን የበሽታውን  ጠባይና አይነት ከሚመራመሩ ፈላስፎች፤   በበሽታው የተያዙትን በሽተኞች ከሞት ለማትረፍ ከሚጥሩት ሐኪሞች  እና ከበሽታው ጋራ በትንቅንቅ ላይ ከነበሩት በሽተኞች  ጋራ እየተወያየ፤ በዘመኑ በሕይወት ከነበሩት ፓትርያርኮች ሊቃነ ካህናት  ከአንድም ጋራ ሳይነጋገር፤ አንዱንም ሳይጠቅስ፤ ቀድሞ የነበሩትን ፓትርያርክና ካህን ብቻ እየጠቀሰ የሆሳዕናውን ዓመታዊ በዓል እንዳከበረው ድርሰቱ ይገልጻል።

እኔም በዚህ ዘመን በዋለው ሆሳዕና ተደራርበው የገጠሙኝን ካይሮቫይረስ   የመሳሰሉትን የህዋሳት ጠባይና አይነት ከሚመራመሩ ፈላስፎች፤   በበሽታው የተያዙትን በሽተኞች ከሞት ለማትረፍ ከሚጥሩት ሐኪሞች  እና ከበሽታው ጋራ በትንቅንቅ ላይ ካሉት በሽተኞች  ጋራ እየተወያየሁ፤ በዘመኔ በህይወት ካሉት ፓትርያርኮች ሊቃነ ካህናት  ከአንድም ጋራ ሳልነጋገር፤ አንዱንም ሳልጠቅስ፤ ቀድሞ የነበሩትን ፓትርያርክ  አቡነ ባስልዮስን፤  ቴወፍሎስን መላከ ብርሃን አድማሱን፤ እነ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤን  አስታወስኩ።

የዘንድሮውን ሆሳዕና በዚህ ትዝታ በማክበር ላይ ሳለሁ፤ መረጃ የሚባለው ሚድያ አምናና ታች አምና ሆሳዕናን እንዴት እንዳከበርከው ከመግለጫ ጋራ  ያቀረበልንን አይተናል። የዚህን አመት ሆሳዕናንስ እንዴትና ከማን ጋራ እንዳከበርከውና በእለቱ ለቅዳሴ የተጠቀምክበትን የጎርጎርዮስን ድርሰት በቅኔው ስልተ ትምህርት አዘጋጅተህ አቀብለን ብላችሁ ስለጠየቃችሁኝ፤ የዘንድሮው ሆሳዕና ደራርብ ለያዘቻቸው ክስተቶች መታሰቢያ ትሆን ዘንድ ይህችን ጦማር በጎርጎርዮስ መጽሀፈ ቅዳሴ አማካይነት በአራት  ጫጭር መግለጫወች አቀረብኩላችሁ።

1ኛ፦የጎርጎርዮስ ቅዳሴ፦በሽታውን ሲቃኘው፦

2ኛ፦የጎርጎርዮስ ቅዳሴ፦ተመራማሪወችን ሲቃኛቸው

3ኛ፦የጎርጎርዮስ ቅዳሴ፦ ሐኪሞችን ሲቃኛቸው

4ኛ፦የጎርጎርዮስ ቅዳሴ፦ፓትርያርክንና ካህንን ሲቃኛቸው

በሆሳዕናዋ እለት የምንጠቀማት የጎርጎርዮስ ቅዳሴ በጎ ርጎርዮስ ዘመን የተከሰቱትን በሽታውን ተመራማሪወችን ሐኪሞችን ፓትርያርኮችንና ካህናትንና ሁሉ ትቃኛለች። በቀርቡ ሞታቸውን ከተረዳሁት ከወንድሜ ከመላከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን ጋራ ባለፈው ዓመት የተነጋገርኩት በትዝታ ጠልፋ ትከታታለች።

አምና የ2011 ዓ/ምን የሆሳዕና በዓል ያከበርኩት ከሊቃውንት ጉባዔ ዓባላት ጋር አዲስ አበባ ነበር። ካረፍኩበት ቦታ ወደ ቤተ ክህነት ስሄድ የቅድስት ስላሴን ቤተ ክርስቲያን እያለፍኩ ነበር። ከደብረ ሊባኖስ ወጥቼ ያስኴላውን ትምህርት የተሳተፍኩበ የብዙ ትዝታየ መዘክር ይህ ካቴድራል ነበር። በወቅቱ የነበሩትን ሊቀ ስልጣናት አባ ሀብተ ማርያም የዛሬው አቡነ መልከጼዴቅ፤ አባ መዓዛ ቅዱሳን (አቡነ ናትናኤል አቃቤ ፓትርያርክ የነበሩት። ) ሌሎችን የትምህርትጓደኞቼን ሁሉ እያስታወስኩ የአንክሮና የተዘክሮ ጸሎቴን አድርሼ ወደ ቤተክህነት እሄድ ነበር። ወቅቱ ሰሙነ ህማማት ነበር። የግሌን ጸሎት ካደረስኩ በኌላ መቃብራቱን እየዞርኩ ሳይ፤  የመላከ ብታቦር ተሾመ ዘሪሁንን  መቃብር አየሁት።

የሞቱ መስሎኝ ደንግጨ አለቀስኩ። ከመላከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን ጋር በቅድስት ስላሴ ካቴድራል በሀዋርያዊ ድርጅት በቤተ ክህነቱ በተሰለፍንባቸው ተቌማት የተካፈልኩት ትዝታ እንባየን አፈሰሰው። እንባየን ጠራርጌ የሁላችንም ጓደኞች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቃውንት ጉባዔ ሄድኩ። ለታሪካዊት ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የደከሙ መላከ  ታቦርን ያህል ምሁርና ባለውለታ ሰው  ማረፋቸውን  ሲነገር አልሰማሁም እያልኩ በመደነቅ ወደ ቤተ ክህነት ግቢ ገባሁና፤  እንዴት ሞታቸው አልተሰማም ብየ የሊቃውንት ጉባዔ አባላቱን ጠየቅሁ። የሊቃውንት ጉባዔ አባላትም በድንገት ከኔ በሰሙባት ቀን ያረፉ መስሏቸው ተደናገጡ።  የሊቃውንት ጉባዔው ዋና ሰብሳቢ ሊቀ አዕላፍ ያዝዓለም ገሠሠና፤ ሊቀ ሥዩማን ራደ አስረስ “ኧረ አለ አልታመሙም አልሞቱም ትላንት በስልክ አነጋግረናቸዋል ” አሉኝ። “ምንማለታችሁ ነው! መቃብራቸውን ባይኔ አይቸው! ከመቃብራቸው ላይ አልቅሽ ነው ወደናንተ የመጣሁ” ብየ መለስኩላቸው።

ተሳሳቀው እኔን ካረጋጉ በኋላ መቃብራቸውን  እራሳቸው እንዳሰሩት ነገሩኝ። ቀጥለውም “በህይወት አሉ አነጋግረናቸዋል” ብለው የስልክ ቁጥር ሰጡኝ። ከሊቃውንት ጉባዔ ቢሮ ሆኘ ደወልኩላቸው። ወደ አሜሪካ ለመመለስ ቀኑ እየቀረበብኝ ነውና መጥቼ ልይዎ ” አልኳቸው። “እኔም መምጣትህን ሰምቼ እስካይህ ቸኩያለሁ። የምኖርበት ሩቅ ስለሆነ አንተ አትድከም። እኔ እመጣለሁ።  ከዚያው ከሊቃውንት ጉባዔ ቢሮ ቆየኝ። ለማነኛውም እንኳን ለአገርህ አበቃህ ” አሉኝ። ቢሮው እስኪዘጋ ጠበኳቸው  አልመጡም። “ምነው ቀጥረውኝ ቀሩ? ብየ በስልክ አነጋገርኳቸው። ከቤተ ክህነት ግቢ ሊያያደርሰኝ ቀጥሮኝ የነበረው ሰው ቀረብኝ” አሉኝ። “ብንገናኝ መልካም ነበር። ካልሆነም እርሰዎ በሞት ቢቀድሙኝ ከመቃብረዎ አልቅሼ እርሜን አውጥቻለሁና አላለቅስም” ካልኳቸው በኋላ “ለምንድነው በህይወት እያሉ መቃብረዎን  በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያሰሩ? የቦታ ሽሚያ ነው ብየ እንደቀልድ ጠየኳቸው። እሳቸውም  መልሰው “እኔ በምሞትበት ወቅት ሁሉም በሞት ጥላ ስር ይሆናል።  መቃብር የሚቆፍርልኝ የሚያለቅስልኝ አይኖርም ። ራሴን ቀብሬ በመቃብሬ ላይ ቆሜ  ለራሴ አልቅሸ አለሁ” አሉኝ።  “እሬሳ አውጭወች የነ ቀኝ ጌታ ንጉሤ ዮፍታሔን፤ የነ መላከ ብርሃን ጀንበሬን እና የነ ፕሮፌሰር አስራትን ሰውነት ከተቀበሩበት መቃብር እያወጡ እያዩ  እንዴት የራሰዎን ሬሳ እዚያው ይቀብራሉ? ብየ ጠየኳቸው። “ይህ ዘመን አይቀጥልም እንጅ። የሚቀጥል ከሆነ ሬሳ አውጭወች የኔን ሬሳ ብቻ በማውጣት የሚወሰኑ አይደሉም” ካሉኝ በኋላ፤ ቀጠሉና “ወደ ኋላ ለምትቀሩት ለቤተ ክርስቲያን ልጆች ወዮላችሁ!  ህዝቡን ወደፈለጉት በመንዳት ላይ ያሉ በቤተ ክህነቱ ሰርገው የገቡ ሁሉ አፈኞች እናንተን የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች በቁማችሁ ይበሏችኋል፤ አንተንማ እንደጀመሩህ ይጨርሱሀል። ለመሆኑ ወዳጅህ አቡነ ማትያስ እንዴት ተቀበሉህ?  ቤተ ክህነቱንስ እንዴት አየኸው? እያሉ ከጠየቁኝ በኋላ “በሰማይ እንገናኝ”   ተባብለን ተሰነባብተን ሁለታችንም ስልኩን ዘጋን።

ወደ አሜሪካ ለመመለስ የመሰነባበቻየ ቀን ስለነበረ፡ በበነጋው ወደ ሊቃውንት ጉባዔ ቢሮ ሄጄ አባላቱን  በጸሎት እንዲሸኙኝ ጠየኴቸው። ጸሎተ ማርያም አድርሰው “እንበለ ደዌ ወህማም ወእንበለ ጻማ ወድካም ያብጻህከ ያብጻሀነ አመ ከመ ዮም” ማለትም፦በሚለው በወቅቱ ጸሎት ተላቀስን ተለያየን።

“እንበለ ደዌ ወህማም ወእንበለ ጻማ ወድካም ያብጻህከ ያብጻሀነ አመ ከመ ዮም” የሚለው “አንተንም እኛንም ከደዌ ከህማም ሰውሮ ለከርሞው ሆሳዕናው በዓል ያድርሰን”  ማለት ነው።

“ይህ ዘመን ከቀጠል የነንጉሤ ዮፍታሔን የነ መላከ ብርሃን ጀንበሬን እና የነ ፕሮፌሰር አስራትን መቃብር የሚያፈልሱ ሰዎች ገና  ወደ ኋላ የምትቀሩትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች እያሰደዱ ይበሏችኌል፤ እኔ ስሞት ሬሳ ተሸካሚና መቃብር ቆፋሪ ስለማይገኝ የራሴን መቃብር ራሴ ቆፈርኩት” ያለኙን የመላከ ታቦርን ንግግር ዛሬ መለስ ብየ ስቃኘው ለካ ቀልድ አልነበረም።

ባለሁበት ባሜሪካና በአውሮፓ መቃብር ቆፋሪ ባሰለቸበት ሬሳ ተሸካሚ በደከከመበት በዚህ ወቅት ማረፋቸውን  ስሰማ፤ መላከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን እንደ አብርሃምና እንደ ነቢዩ አሞጽ ነበሩ ብየ አሰብኩ።  “እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሃም እሰውራለሁን”(ዘፍ 18፡17) ብሎ ለአአብርሃም የተናገረ  አምላክ፤ “እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለአገልጋዮቹ ሳይገልጥ ምንም ነገር አያደርግም”(አሞ 3፡ 7) ብሎ በነቢዩ  አሞጽ የተናገረው አምላክ፤ ለመላከ ታቦር ተሾመ ይህችን ዓለም በሚለቁበት ወቅት የሰው ልጅ በካሮናቫይረስ እየታነቀ ማለቁን አሳይቷቸው እንደነበረ ተረዳሁ።

ከዚህ በፊት በ2002 ዓ/ም የሲኖዶሱ ሊቀ መንበር የነበሩት መጋቤ  ብሉይ ሰይፈ የሲኖዶሱን እርቅ ለመደራደር ዋሸንግተን በመጡ ጊዜ፤ አቡነ አብርሃም ባደረጉት የፍልሰታ ቅበላ እራት ላይ “ሰላም ይፈጠራል ብለን መጣን ሳይሆን ቀርቶ  የመሬትን ትቢያ ከእግራችን አራግፈን ይህችን መድር ለቀቅናት” ብለው ሀሙስ ማታ ተናግረው፤ ቅዳሜ ከኢትዮጵያ ሲደርሱ ይህችን ዓለም በሞት ለቀዋት መሰናበታቸው ታይቷቸው እንደተናገሩ አድርጌ የተረዳሁት የተደገመብኝ መሰለኝ።

የመላከ ታቦርን ነቢይነት በአዕምሮየ ቋት ይዠ በመገረም ላይ ሳለሁ፤ በማገለግልባት ቤተ መቅደስ  የጎርጎርዮስን ድርሰት መጽሐፈ ቅዳሴውን አብረውኝ ከተሳተፉት ሁለት ኦርቶዶክሳውያን ጋራ ፈተሽኩት። ጎርጎርዮስ በሕይወት የሌሉትን ፓትርያርኮች አብርሃምንና መልከ ጼዴቅን እያስታወሰ ከዘመኑ ተመራማሪወች ጋራ እና ሀኪሞች ጋራ እየተነጋገረ እንዳከበረው፤ እኔም በሕይወቴ ዘመን የሌሉትን ፓትርያኮች አቡነ  ባስልዮስን እና  አቡነ ቴወፍሎስን እያሰብኩ፤ ከሳይንስ ተማሪወችና ከሀኪሞች ጋራ በዘመኑ ስለተከሰተው ህዋስ (ካሮናቫይረስ) እየተነጋገርኩ እንደ ጎርጎርዮስ  አከበርኩት። አሁን በዘመናችን ከተከሰተው ከበሽታው በመጀመር ወደ መጽሐፈ ቅዳሴው ወደጎርጎርዮስ ድርሰት እሻገራለሁ

1ኛ፦የጎርጎርዮስ ቅዳሴ ባካቢ የነበረውን ሕዝብ ሲቃኝ  

ጎርጎርዮስ “ቡሩክ እግዚ በኩሉ ግብሩ ወስቡህ ጥቀ በኩሉ ንባበ በሀውርት ወልሳን ዘአምጸአን እምሀበ ኢሀለዎ ሀበ ሀለዎ አፍቂሮ ኪያነ”(ሃ 36፡2)። በማለት “በዓለም ቋንቋወች የምትመሰገን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣሀን በስነ ፍጥረትህ የምትደነቅ ፤ በተለያዩ ሥርአተ አምልኮ በደቂቀ አዳም የምትመለክ እያለ”   እግዚአብሔርን በማድነቅ በቅዳሴው የተዳሰሱትን ወደትኩረት  ይስባል።

“ንዑ አኀውየ እለ ትፈቅዱ ትርአዩ መዋዕለ ሠናያተ ንክላእ ልሳነነ እምእክይ ወከናፍሪነኒ ከመ ኢይንብብ ጉሁሉት”(ቅ 37 ፡16) ። ያላችሁበትን ዘመን ለመፈተሽ ፈቃደኞች የሆናችሁ በተፈጥሮና በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው አሉባልታችሁን ትታችሁ ስላለንበት ዘመን ወደፊት ስለሚገጥመን ዘመን እንነጋር ኑ”  እያለ ደቂቀ አዳምን ይጋብዛል።

“ወናእትት ጽልመተ ኃጢአት እምሥጋነ ወነፍስነ ወመንፈስነ ከመ ዘይትአተት ጽልመተ ዛህል እምነ አረር። ወሐጺን ወብርት በእሳት ወዐቃቂር ውዕያት. . . ( ሃ 37፡18) ጠበብቶች ማስወገድ በሚችሉበት ጥበብ በእሳት በቅመም (ኬሚካል)ዝገትን ከብረት እንደሚያስወግዱ፤  በሥጋችን የገባውን ጽልመተኃጢአት (invisibl viros) እናስወግድ“  እያለ ይጋብዛል።

የስነ ፍጥረት ሊቃውንት ሀኪሞች፤ የነብያትን ምክር የክርስቶስን ምሳሌነት እየጠቀሱ የሚናገሩትን እየተቃወሙ “ተሳሳሙ ተጨባበጡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሂዱ ጸበል ጠጡ“ በሚል ምጽድቅ እንዳንዘነጋ  “ንህነሰ አብደርነ ሞተ እምህወት ወሀሳረ እምነ ተድላ በፈቃድነ ወበተወክፎ አሰፍጦተ ጸርነ ወወደቅነ በፍትወትነ ውስተ ደውያት ወይወስድ ውስተ ኩነኔ ዘአልቦቱ ማህለቅት”(36፡14) ይላል። ይህም ማለት፦የኔ ቢጤ ደካሞች ከህይወት ሞትን፤ ከደስታ ስቃይን መረጥን፤ የሚወረንን ጠላት ወደን ፈቅደን ተረከብነው ፍጻሜ በማይኖረው ግንኙነትም ተቆላለፍነው።

የተመራማሪወችን ምክር ቸል የሚሉትን፤ ከሀኪሞች መድኃኒት ራቁ የሚሉትንም ለብዙ ወገን ሞት ምክንያት እንዳይሆኑ “ሶበ ይደዊ በእንተ ፈውሰ ዚአሁ  እምከመ ጠየቅነ ዘንተ ንትመጠው ፈውሰ እምእደ ጠቢብ መሀሪ ዘይትራዳእ ነፍሰነ ወመንፈሰነ ወሥጋነ””(ሃይ 37፡10)እያለ ይመክራቸዋል። “በታመመን ጊዜ ስለ በሽታው ለመረዳት እንጣር። ስለ በሽታው ከተረዳንና ካወቅን እኛን ለማዳን ከሚታገሉት ሐኪሞች መድኃኒቱን እንቀበል። እያለ ስለ እግዚአብሔርና  እና ስለ ስነ ፍጥረቱ ያልተገነዘቡትን ግብዞችንም ያስጠነቅቃል።

2ኛ፦የጎርጎርዮስ ቅዳሴ  ተመራማሪወችን ሲቃኝ

”ወሶበ ይትረክበ  ጠቢብ ወምሁር ወፍልሱፍ ማእምር ዘያስተራክብ ሙስናሆሙ በዘያሴኒ ወያአትት እምኔሆሙ ሙስና ዘቦአ ለእሌሆሙ እምነ መሬት ወይመይጦሙ ሀበ ጽርየት ወያግህስ ርስሀተ ዘቦአ ላእሌሆሙ ወይሬስዮሙ ወርቀ ወብሩረ”(37፡9)አለ። ማለትም፦ ሰው በፈጠረው ስህተት  ጤናውን እንድትነሳ መሬት ላይ የበቀለችው  አሚከላ ሰው በመሬት ላይ እስካለ ድረስ መልኳንን ጠባይዋን እየቀየረች ትከሰታለች። ህዋሷ በተከሰተችበት ወቅት የሚገኝ  ምሁር ፈላስፋ ካነቀችው ሰው ጎሮሮ እየመነጨቀ ይጥላታል።

ምሁሩ ከክህብረተ ሰቡ ቀደሞ ብሎ ቢነቃና ዘግይቶ ቢረዳትም፦ የመረዳቱና የእውቀት አቅም በእግዚአብሔር ዘንድ ኢምንት መሆኗን “ሥውር ውእቱ እምህሊና ኩሎሙ መላእክት አልቦ ዘየአምሮ መላእክት ወአልቦ ዘየአምር ለህላዌሁ ወአልቦ ዘይሄልቆ ዘለሀኮ በእዴሁ” (11)እያለ  ያሳስባቸዋል።

ለአጽንኦተ ነገር ይቀጥልና “ግሩም እምግሩማን ወልዑል እምልኡላን” “አልቦ ዘይወጽእ ወዘይገብእ እንበለ ውእቶሙ ግሩማነ ራእይ እለ ስድስቱ ክነፊሆሙ። ወእንተ ኩለንታሆሙ ምሉዓነ አዕይንት“ እያለ ማንም ፈላስፋ የግዚአብሔርን ጥበብ እስከ ጥግ መጨረሻ ሊረዳ አይችልም ፤ ሥጋ ለባሽ የሆነ ሰው ይቅርና ሁለንተናቸው ዓይን የሆኑት ግሩማን ኪሩቤል አያውቁም። የፈጠረውን የሚቆጥርና የሚሰፍር የለም።

ከሙሉነቱም የተነሳ “እምሆሳዕናሁ አርአየ ጸጋ ወኃይለ ወሪዶ እምልዑል መንበሩ እንዘ ኢያንቀለቅል መሰረተ ቤቱ” ከመንበሩ ሳይነቀሳቀስ በምልአተ መለኮቱ ጸጋን ምልዓትን እውቀትን ጥበብን ህይወትን መድሀኒትነትን ለተመራማሪወች ያሳያል።   እያለ የፈጣሪን ሙሉነት የተመራማሪወችን  ጎደለነት ይነግራቸዋል።

በዘመን በአካልና በቦታ የተወሰኑ ፈላስፎች አቅማቸውን እየታዘቡ እግዚአብሔር የሚገለጽበትን የሚደነቅበትን ስነፍጥረትንና የአሚከላዋን ዲቃላ እያጠኑ እንዲታገሉ፤ በሽተኞች በአምላካቸው ላይ ያላቸውን እምነት ሳያላሉ ለጥበበኞች የተገለጸውን መድሀኒት እንዲጠቀሙ እየመከረ ወደ ሀኪሞች (ዐቃቤሥራይ)ፊቱን ያዞራል።

3ኛ፦የጎርጎርዮስ ቅዳሴ   ሐኪሞችን ዐቃብያነሥራይ)

ጎርጎርዮስ የክርስቶስን ዘላለመዊ አዳኝነት (ሆሳዕናነት)በአንጻርነት “ኅድግሰ  ዐቃቤ ሥራይ ዘይፌውስ ህማመ ነፍሳት”  እያለ የክርስቶስን ፈዋሽነት በመጥቀስ  ለምድራውያንና  ለሥጋውያን ሀኪሞች መድኃኒት መስጠታቸውን በሽተኞችም መፈወሳቸውን ያምኑ ዘንድ “ዐቃቤ ሥራይሂ ዘሥጋ ሶበ ይበውእ ሀበ ድውየ ሥጋ ዘይዔዝዞ ከመ ይትአቀብ  እምነ መባልእት እኩያት ወያሰትዮ ቆጽላት መሪራተ ወአቃቂረ  ዘዕጹብ ምረሩ ወፍጉግ ጼናሁ ከመ ያስተራክብ  ቦቱ ህዋሳተ ዘሀሎ ውስተ ሥጋሁ።  ለውእቱ ድውይ። ወለእመሰ ደዌሁ ዕጹበ ወኢትከሀል ይትፈወስ ዘእንበለ ዳእሙ ይስጥጥዎ  በሐጺን አው ይምትርዎ አባሎ አው ይግምድወ እምሥጋሁ አው ያውእይዎ በእሳት(37፡4᎗6)” እያለ ይመክራቸዋል።  ይሞክራል።

ይህም ማለት፦ምድራዊ ሀኪም ወደቤተ ህሙም ሲገባ፤   ከማይጠቅሙ ምግቦች እንዲገለል በሽተኛውን  ያስጠነቅቃል። ። በሰውነቱ የገባውን ህዋስ በሚያቀብለው መድሀኒት ይፈውሳል። ህመምተኛው በመድሀኒት የማይፈወስ ከሆነ፤ ሀኪም በስለት ቀዶ ጥገና ይደረግለታል። የእሳት ትኩሳትም ይጠቀማል“ እያለ ” እያለ የሀኪሞችን ተልእኮ ይገልጻል።

”ሶበ ተመየጥከ  ሀበ ዝክረ ፈውሳት ዘይትአተት ቦሙ ርስሀት ዘቦአ ላዕለ ኩሉ ፍጥረታተ ብርት ወዐረር ወሀጺን እምዘረከቦሙ እምነ ህምዝ ዐበይት ዘያበውእዎ ውስተ ዝንቱ ርስሀት ከመ ያውጽኦ ዘከመ ያበውኡ ፈውሳተ ዐበይተ ሥጋ እጓለ እመህያው። (10) እያለ  በቀጠለው ንግግሩ፦  አምላክንና ስነፍጥረቱን በሚገባ ሳይገነዘቡ ስለ መንፈሳዊም ሆነ ስለ ስነ ፍጥረት በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ለመምህርነት የተሰለፉ ሰዎች  ጎርጎርዮስን ከበው ያስቸገሩት ይመስላል።   ይህም ማለት፦ሰው በታመመ ጊዜ ዓቃብያን ሥራይ  በሚሰጡት  መድሀኒት የመርገሟ አሚከላ ህዋስ በተለያዩ  ንክኪወች በሰውነቱ ካስገባቸው መርዝ እንደሚድን  ብታውቅ ከጭፍን እምነትህ ተላቀህ ብሽተኛውን ወደ ሀኪም እንዲሄድ በረዳሀው ነበር።

“ቶስህ ማየ ምስለ ወይን ነፋሰ ምስለ እሳት ወማየሂ ዘምስለ  መሬት ከማሁ ቶስህ ድካመ ዚአነ ውስተ ጽንአ መለኮትከ ወደምር ካዕበ ህማመ ዚአነ ውስተ ህማመ መስቀልከ” 103 ። በማለትም መሬት በምታበቅለው ህዋስ በመነደፍ ላይ ያለውን የደቂቀ አዳምን ትክለ ሰውነት እየዘረዘረ በተዋህዶ ምሥጢርም ዘላለማዊ መዳንን እንዳገኘ አካሚውም  ታካሚውም እንዲረዳዱ እንዲግባቡ በመፈንስና በአካል እንዲበረታቱ “አብጥሎ ለዘያሜክረነ ወስድዶ እምኔነ ወገስጽ ሁከታቲሁ ዘተከለ ዲቤነ ወብትክ እምኔነ ምክንያተ እንተ ትወስዶም ውስተ ኃጢአት ወባልሀነ በኃይልከ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ  እግዚእነ” 85 እያለ  ይመክራል።

ይህም ማለት፦ “በሀኪሞቹ አድረህ የሚፈታተነን ህዋስ አስወግደው፤ በህሊናችንና በመንፈሳችን የተከለብንን መሸበርን መርበድበድን መንቀጥቀጥን ነቃቅለህ ጣልልን እያለ በተልይ በሽተኞችን ያበረታታል።

“ወአመነ በትንሳኤሁ ፍጹም ምሥጢር” ሀኪሞችም ታካሚወችም በትንሳኤ ዘጉባዔ  ሙታንን ከመቃብራቸው የምታስነሳ አምላክ፤ ህሙማኑ ቫይረሷ ካስተኛችባቸው አልጋ ተወፈውሰው ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱ እናምናል እንዲለ በሚያጽናና ምክሩ ከሀኪሞች ጋራ ያለውን እዚህ ላይ ይገታና፤  ጥንት ወደ ነበሩት ፓይርያርኮች ወደ እነ አብርሀምና መልከ ጼዴቅ ፊቱን ያዞራል።

4ኛ፦የጎርጎርዮስ ቅዳሴ ፓትርያርክ  አብርሃምንና ካህኑን ሲቃኝ  

ጎርጎርዮስ በደቀደሙት ፓትርያርኮች በአብርሃምና በመልከ መልከ ጼዴቅ ላይ ያተኮረው ለሆሳዕናው ምሥጢር ተስማሚወችና የምሳሌነታቸውም አስተማሪነ ለተከሰተው ቀውስ  የሚጠቅም መሆኑን የተረዳ ይመስላል።

ጎርጎርዮስ “ቀዳማዊ ዘእንበለ ጌሰም፤  ወደኃራዊ ዘእንበለ ትማልም ብሉየ መዋዕል ዘእንበለ ዮም ወጌሰም”(22)  እያለ፦ እግዚአብሔር የህያዋንና የሙታን አምላክ እንደሆነና  ዘላለማዊነቱን  ይናገራል። የአብርሃምን ፓትርያርክነት የመልከጼዴቅን ካህንነት ከሆሳዕናው በዓል ጋር አገናኘው። ከአብርሃም በመጀመር መልከጼዴቅና አብርሃም እነማንና ምን አይነት ፓትርያርክና ካህን እንደነበሩ ይገልጻቸዋል።

አብርሃም የእግዚአብሄርን ጥሪ ተቀብሎ፤ የብዙ ህዝብ አባት ለመሆን ከሥጋ ዘመዶቹ ከጎሳው ተለይቶ ቆርጦ የወጣ ፓትርያርክ ነበር። በሱና በሎጥ እረኞች መካከል ጸብ ሲፈጠር፤  ራሱን ከስስት  ስግብግብ ባህርይ በማለየት  “እኛ ወንድማማች ነን በመካከላችንና በእረኞቻችን መካከል ጠብ እንዳይነሳ እለምንሀለሁ። አንተ ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ መሄድ እችላለሁ”( 13፡8᎗10  )እያለ ከንብረት ከገንዘብ ይልቅ ለሰው ክብርና ፍቅር ቅድሚያ መስጠትን በተግባር ያስተማረ የፓትርያርክነትን ባህርይ ያሳየ አባት ነበር።

“ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ልዑል እግዚ የዘረጋሁትን እጄን፤ ባንተ ስጦታ አላረክስም”(22)እያለ የፓትርያርክነቱን ማእረግና ቅድስና ምድራውያን ፈላጭ ቆራጮች ባቀረቡለት ብዝበዛ ያላረከሰ  ቅዱስ ፓትርያርክ ነበር። በፓትርያርካዊ ፍጹምነቱም፤   ባንዣበበው መቅሰፍት ማንም እንዳይጎዳ  “እነሱን ክምታጠፋ ስለነሱ እኔ አፈር አመድ ልሁን እያለ ለጠላቶቹ ለሰዶምና ለገሞራ የተማጸነና የማለደ ርህሩህ ፓትርያርክ ነበር (18፡27)።

ጎርጎርዮስ በዘሙኑና ባካባቢው በህዝቡ መካከል በየዙፋናቸው ከተቀመጡ ፓትርያርኮች አንድ ሳይጠቅስ  የፓትርያርክነቱ ባህርይ ከክርስቶስ  አዳኝነት (ሆሳእናነት)ጋራ ስለተስማማ  “ያጽድቆሙ ለጊጉያን ያንጽሆሙ ለርሱሀን ይሚጦሙ ለስሁታን ሆሳዕና በአርያም”(50)እያለ ባከበረው በሆሳዕናው በዓል ላይ  አብርሃምን ጠቀሰው ። ከዚህ ቀጥለን ካህኑን መልከ ጼዴቅን እንመልከት።

መልከጼዴቅ ክርስቶስን በትክክል የሚገልጽ የበረከት የጽድቅና የድል ካህን ነበረ። በዘበኝነትና በክብር ጠባቂነት የሚያገለግለው የሚጠብቀውና ወሬ የሚያቀብለው  ከጎሳው ከዘሩ ያሰለፈው አርዌበትር ተሸካሚና የማእድ ተካፋይ  አልበረውም።   አብርሃም የድል በረከት ተጠምቶ የእግዚአብሔር ካህን ፍለጋ በወጣበት ወቅት መልከጼዴቅን አገኘ ።  ሱባዔ የምትገባበት የምትደበቅበትና የምትሸሽበት ጊዜ አይደለምና   የእግዚአብሄር  ሰው ሆይ!  ውጣ ” እያለ  መልከጼዴቅን ቀሰቀሰው። ቅዱሱና ዘር አልባው የበረከትና የድል ካህን መልከ ጼዴቅም የታላቁን የአብርሃምን ጥሪ ተቀብሎ፤ “ኢትፍራህ እስመ እግዚ ዘፈነወከ ይቤለኒ ይመጽእ ሀቤከ” ማለትም፦ እግዚአብሔር  ወዳንተ ልኮኛልና  አትፍራ አይዞህ በርታ እያለ አብርሃምን እያጽናና ወጣ (80)

ጎርጎርዮስ በስነ መለኮትና ስነፍጥረት ተማሪነቱ የስነፍጥረትን እና የሰውን ጻእርና ገአር ተመለከተ።  ለሆሳዕና በደረሰው መጽሐፈ ቅዳሴ መሬት ታብቅልብህ የተበላቸው አሚከል ተናዳፊወችን  ህዋሳት እንደምታዘምትበት ተረዳ። የሰው ልጅም የሚዘምቱበትን ህዋሳት እንዲቋቋም የታዘዘውን የተፈጥሮ ህግ የተገንዝበ እና ሀላፊነቱን የተወጣ ሊቅ ነበር። ክርስቶስ በምትመጣው መንግስቱ የማትኖር ቦታ እንደሌላት ቢያደርጋትም፤ በዚህ ዓለም እስካለን ድረስ  በሰውና በአሚከላዋ ዲቃላ መካከል ያለው ትንቅንቅ የማይቆም መሆኑን በመጽሐቅዳሴው ዳሰሰው። አሚከላዋም ቃል ኪዳኗን ጠብቃ እየተቀያየረች በየዘመኑ የሰውን ልጅ  ትወጋዋለች። ደቂቀ አዳምም በምሁሮቹ  ፈላስፋ አማካይነት ነቅቶ መታገል እንዳለበት በስነ መለኮትና በስነ ፍጥረት ትምህርቱ ጎርጎርዮስ ያስገንዝባል።

በተረፈ ካሮናቫይረስን የመሳሰሉትን የአሚከላዋ ውላጆች ተሀዋስያን፤ በረቂቅ መሳሪያቸው በማደን ላይ ላሉት ጠበብቶቻችን፤  ህዋሷ አንቃ ከያዘቻቸው ከሰዎች ጉሮሮ ላይ  እየመነጨቁ የሚጥሉበትን የበለጠና እጅግ የላቀ እውቀት ጥበብና የስነ ልቡና ልዕልና ለሀኪሞቻችን ይስጥልን፤ ለህዝብ በረከት ጽድቅና ድል የተሰለፈ ክርስቶስን በትክክል የሚገልጽ አብርሃምን የመሰለ  ፓትርያርክ፤  መልከ ጼዴቅን የመሰለ ዘር አልባ የእግዚአብሔር ካህን ለቤተ ክርስቲያናችን ያስነሳልን።

የዛሬ ዓመት የምናከብረውን የሆሳዕና በዐል በተረጋጋ በፍስሀና በሀሴት ለማክበር ያብቃን!

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

[email protected]

ሚያዝያ 5 ቀን  2012 ዓ/ም