በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት የሰባት ወጣቶች ህይወት አለፈ

( ኢዜአ ) በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ ዲቢቢሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በዮሃንስ ቤተክርስቲያን ለጊዜው በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ሰባት ወጣቶች ሞተው መገኘታቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ ።
የመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት በአንድ አነስተኛ ክፍል ውስጥ ሞተው ከተገኙት ሁሉም እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሲሆኑ ከሟቾቹ መካከል አንዷ ሴት ናት።
ትላንት ከሎሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ሟቾቹ በተገኙበት ወቅት የመብራት አገልግሎት የተቋረጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጀነሬተር እንደተለኮሰ ገልጸው አደጋው ከጄኔሬተሩ ጭስ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ እየተጣራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከአደጋው ጋር በተያያዘ በአካባቢው 11 ግለሰቦች ተጠርጥረው መያዛቸውንና የማጣራት ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሟቾቹ አስከሬን ለተጨማሪ ምርመራ ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል መላኩን የገለጹት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ሁሉም ቤተ ዕምነቶች ዝግ መሆናቸውንና አማኞችም በቤታቸው አምልኮ ማድረግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ክስተቱ እንዴት እንደተፈጠረና ወጣቶቹ እንዴት ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ሊገቡ እንደቻሉ እያጣራን ነው ያሉት ኮማንደሩ ጉዳዩን የሚያጣራ ግብረሃይል ተቋቁሞ የማጣራት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ ሁሉም ሰው ርቀቱን ጠብቆ በዓሉን ማክበር አንደሚገባው ያስታወቁት ኮማንደር አስቻለው በቤተክርስቲያኑ የታየው ነገር አስደንጋጭና ትምህርት ሊወሰድበት አንደሚገባም አሳስበዋል።